[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]
– ምን ችግር አለበት?
– ችግሩ ዕዳ የሚለው ቃል ላይ ነው።
– ዕዳ የሚለው ቃል ምን ችግር አለበት?
– ለእኔም ብዙ ግልጽ አልሆነልኝም ግን…
– ግን ምን?
– መንግሥት አልወደደውም።
– ለምን?
– ከፍተኛ ዕዳ ያለበት መንግሥት ስለሆነ፡፡
– ያው አይደለም እንዴ?
– ምኑ?
– ተረጂነት የሚለው ቃል፣ ከዕዳ ወደ ተረጂነት መቀየሩ ምን ለውጥ ያመጣል?
– ያው ነው ግን…
– ግን ምን?
– በቀጥታ መንግሥትን አያመለክትም።
– እንዴት ማለት?
– ዕዳ የሚለው ቃል ከመንግሥት ዕዳ ጋር ሊገናኝ ስለሚችል አልተወደደም።
ዕርዳታ ግን ለመንግሥት አይደለም የሚቀርበው።
– እና ለማነው?
– ለተረጅዎች።
– ተረጅው ማነው?
– ሕዝብ፡፡
– እህ…. አሁን ገባኝ።
– ምንድን ነው የገባሽ?
– ከዕዳ ወደ ምንዳ የሚለው ንቅናቄ ምንን ታሳቢ አድርጎ እንደተጀመረና ለምን እንዳልተፈለገ ገባኝ።
– ምንን ታሳቢ ተደርጎ ነው የተጀመረው?
– ፓሪስ ክለብን።
– ከፓሪስ ክለብ ምን ታሳቢ ይደረጋል?
– ዕዳ ስረዛ፡፡
– እርግጥ ነው ዕዳ ስረዛ እንደሚኖር ታሳቢ ተደርጎ ነበር።
– ዕዳው ተሰርዞ ቢሆን ኖሮ በገባነው ቃል መሠረት ከዕዳ ወደ ምንዳ ተሸጋገርን ሊባል ነበር ግን አልሆነም።
– አልሆነም ማለት?
– አልተሳካም ማለቴ ነው።
– እውነት ነው፣ ለጊዜው አልተሳካም።
– ስለዚህ ከራሳችሁ አወረዳችሁት።
– ምኑን?
– ንቅናቄውን ነዋ?
– ወዴት እናወርደዋለን?
– ወደ ሕዝብ ነዋ፡፡
– ምን ብለን?
– ከተረጂነት ወደ ምርታማነት!