Home Back

ሩሲያ የኅዋ ጦር መሣሪያ በአሜሪካ ሳተላይት ትይዩ አመጠቀች

voanews.com 2024/6/29
በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የፕሬስ አገልግሎት የተለቀቀ ፎቶ፤ እአአ ግንቦት 17/2024
በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የፕሬስ አገልግሎት የተለቀቀ ፎቶ፤ እአአ ግንቦት 17/2024

“የኅዋ ጦር መሣሪያ ሳይሆን አይቀርም” ያለውን ሳተላይት ሩሲያ ማምጠቋን የአሜሪካ መከላከያ መ/ቤት (ፔንታጎን) አስታውቋል። ሩሲያ ያመጠቀችው የጦር ሳተላይት በአሜሪካ መንግስት ሳተላይት ተመሳሳይ ምህዋር ላይ መሆኑንም ፔንታጎን ጨምሮ አስታውቃል።

“ሩሲያ በእኛ ግምገማ የኅዋ ጦር መሣሪያ ወደ ታችኛው የመሬት ምህዋር አምጥቃለች። ይህም ሌሎች በተመሳሳይ ምህዋር የሚገኙ ሳተላይቶችን ማጥቃት የሚችል ነው” ብለዋል የፔንታጎን ቃል አቀባይ የሆኑት ሜጄር ጄነራል ፓት ራይደር።

ባለፈው ሣምንት የመጠቀው “የሩሲያ ፀረ-ኅዋ የጦር መሣሪያ፣ የአሜሪካ መንግስት ሳተላይት በሚገኝበት ተመሳሳይ ምኅዋር ላይ ነው” ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል።

ዋሽንግተን ጉዳዩን መከታተል እንድምትቀጥል እና በኅዋ ያሏትን ንብረቶችንም እንደምትከላከል ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

አሜሪካ በኅዋ ላይ የጦር መሣሪያ ማኖር ትሻልች ስትል ሞስኮ ትላንት ማክሰኞ ክስ አሰምታ ነበር። ይህም ሩሲያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኅዋ ላይ የጦር መሣሪያ እንዳይውል ስትል ያነሳችውን ሃሳብ አሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ ማድረጓን ተከትሎ ነው።

“ኅዋ ከጦር መሣሪያ ነፃ እንዲሆን እንደማትሻ አሜሪካ በድጋሚ አሳይታለች” ሲል የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫ አስታውቋል።

ባለፉት ወራት ውስጥ፣ ሁለቱ ሃገራት በኅዋ ላይ የጦር መሣሪያ ማኖር በመሻት አንዱ ሌላውን ሲከሱ ቆይተዋል።

People are also reading