Home Back

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ethiopianreporter.com 2024/7/6
spot_img
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት የተገነቡ ሕንፃዎችና መመርያዎች ከፊል ገጽታ

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

 ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገሮች በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጭምር መነጋገሪያ የሆነው ይህ ረቂቅ አዋጅ፣ በውስጡ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል፡፡

በስምንት ክፍሎችና በ57 አንቀጾች ተሰናድቶ የቀረበው አዲሱ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ፣ ከቀድሞው የፀረ ሙስና አዋጅ በይዘቱም ሆነ በአድማሱ የሰፋ መሆኑ ይነገራል፡፡ አዋጁ ገና ከወዲሁ በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነው በብዙ ጉዳዮች አዳዲስ የሕግ ድንጋጌዎችን ይዞ በመቅረቡ ነው፡፡

 አዲሱ አዋጅ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ሀብትን በሚመለከት ሰፋ ያለ ትንተና ይዞ ቀርቧል፡፡ አንድ ሰው ከሕጋዊ ገቢው ውጪ ለሚያገኛት እያንዳንዷ ገንዘብ ከሕጋዊ ምንጭ መገኘት አለመገኘቱን የሚያረጋገጥ ደረሰኝ እንዲያቀርብ መጠየቁ፣ አዋጁን ጠጠር ያለ ነው እያስባለው ነው፡፡ ውጭ ካለ ዘመድ የተላከም ሆነ እንደ ቢትኮይን ካሉ ዲጂታል የገንዘብ ምንጮች የሚገኝ ገቢ ሕጋዊነቱ መረጋገጥ እንደሚኖርበትም ይደነግጋል፡፡

‹‹ገንዘብ የሚያስገኙ ወንጀሎች የሚፈጽሙት ወንጀል ፈጻሚዎቹ በወንጀሉ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ነው›› ሲል አዋጁ፣ ገንዘብ የሚያስገኙ የወንጀል ድርጊቶችን ይዘረዝራል፡፡ የሙስና ወንጀሎች፣ ጉቦ መቀበል፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ የተከለከሉ እፆችን ማዘዋወር፣ የሐሰት ገንዘብ ማተም፣ ሕገወጥ ሐዋላ፣ የታክስና የኮንትሮባንድ ወንጀሎች እያለም በዝርዝር ያመለክታል፡፡

 በዚህ የወንጀል መዝርዝር ሥር እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገሮች የሚፈተኑባቸው ከንግድና ግብይት ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ስለመካተታቸው የተብራራ ነገር የለም፡፡ በወጪና ገቢ ንግድ ሒደት በኤልሲ ማስከፈት ስም ብዙ ገንዘብ እንደሚመዘበር ይነገራል፡፡ ገበያ በመስበር ወይ እጥረት በመፍጠር፣ እንዲሁም ምርትና አገለግሎቶችን በማስወደድ፣ በማርከስ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አሻጥር እንደሚፈጸምም ይነገራል፡፡ እነዚህን ጨምሮ ሌሎችም ከንግድና ግብይት ጋር የተያያዙ ሕገወጥ የጥቅም ማግኛ መንገዶች በዚህ አዋጅ ስለመሸፈናቸው የተብራራ ነገር የለም፡፡

የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያስገኙ ወንጀሎች ለፈጻሚዎቹ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ በአገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ዕድገት ላይ የሚያሳርፉት ተፅዕኖ እጅግ አደገኛና ውስብስብ መሆኑን በመጥቀስ ነው አዋጁ የሚነሳው፡፡

ከወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ መርሆዎች መካከል የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችንና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ፣ ወይም ለማስተዳደር የሚያስችል ግልጽና ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንደሚሆን መቀመጡን አዋጁ ይጠቁማል፡፡ በፖሊሲው ቁጥር 3.16.3 ላይም ስለንብረት ማገድና መውረስ መካተቱንም አዋጁ ይጠቅሳል፡፡

ከዚህ በመነሳትም አንድ ወጥና ራሱን የቻለ ሕግ ለማዘጋጀት እንደተፈለገ ያትታል፡፡ በአዋጁ የተካቱት የንብረት ማስመለስና አስተዳዳር ድንጋጌዎች በተለያዩ የሕግ ሰነዶች ተበታትነው የሚገኙ የሕግ ድንጋጌዎችን ወደ አንድ በማሰባሰብ መቅረባቸውንም ያክላል፡፡ አዋጁ ያስፈለገውም የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማስተዳዳር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ለማበጀት እንደሆነ ይገልጻል፡፡

አዋጁ ይህን ከመነሻው ቢልም ነገር ግን ከታሰበው ሕገወጥ ሀብትና ንብረትን የመቆጣጠር ዓላማው ባለፈ ለሌሎች አሉታዊ ዓላማዎች የሚውልበት ዕድል እንደሚሰፋ በርካቶች በሥጋትነት እያነሱት ይገኛል፡፡ በዋናነት ደግሞ ሕጉ ዜጎችን ለማጥቂያነት ይውላል የሚለው ሥጋት ይሰማል፡፡

ስለሕጉ ጥቅም ሐሳብ እንዲሰጡ የተጠየቁ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሕግ ባለሙያ፣ ‹‹አዋጁ በግልጽ በሕግ የመገዛትን መርህ (Principle of Legality) ይጥሳል፤›› ብለው ‹‹አንድ ሕግ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ባለው የጊዜ ወሰን ብቻ ተፈጻሚነት ይኖረዋል (Principles of non Retroactivity) የሚለውን መርህም ይጥሳል›› ብለዋል፡፡ የሕግ ባለሙያው ሐሳባቸውን ሲያሳርጉም፣ ‹‹አዋጁ በብዙ መንገዶች ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ሌሎች በአዋጁ ላይ አስተያየት የተጠየቁ የሕግ ምሁራን በበኩላቸው ሕጉ የወጣበትን መንፈስና አጠቃላይ ሊውል የታሰበበትን ዓላማ በአዋጁ፣ እንዲሁም የአዋጁን ሰነድ ተደግፎ ከቀረበው መግለጫ ባለፈ ያሉ ጉዳዮችን መፈተሽ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ያም ቢሆን ግን በረቂቁ ሰነድ ተከትቦ በቀረበበት መንገድ ሕጉ ወደ መሬት ይውረድ ከተባለ ግን ብዙ ችግሮች ሊፈጥር እንደሚችል ነው ሥጋታቸውን የገለጹት፡፡

የሕግ ባለሙያዎቹ ሕጉን የሚያስፈጽመው ዞሮ ዞሮ ሰው መሆኑን በመጥቀስ፣ የሚያስፈጽመው አካል ንፅህና ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ተቋማቱ ድረስ ያለው ዕውቀት፣ አቅም፣ ብቃትና ሥነ ምግባር መፈተሽ እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡   

አዲሱን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የሕግ ባለሙያው አደም ካሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሕጉ እንደ ሕግ የተረቀቀበት መንገድ ወይም በውስጡ የያዛቸው ይዘቶችን በተመለከተም ቢሆን ብዙም ችግር እንዳልታያቸው ነው የገለጹት፡፡ ኢትዮጵያ ሕግ ሳይሆን የሚያስፈልጓት የወጡ ሕጎችን በአግባቡ የሚያስፈጽሙ የፍትሕ ተቋማት እንደሆኑ በመጥቀስ የፍትሕ ተቋማቱ ላይ ለውጥ እንዲመጣ መሥራት እንደሚሻል አሳስበዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በመሠረታዊነት ችግሩ በሕግ መገዛት ከሚባለው ነገር ጭምር ማለፋችን ነው፡፡ ከሕግ የበላይነት ወደ በሕግ መግዛት ተሸጋገርን ተብሎ ያኔ ቅሬታ ይሰማ ነበር፡፡ አሁን ግን በሕግ የመግዛቱ ነገርም ሁሉ የለም፤›› በማለት ነው የፍትሕ ሥርዓቱ ብልሽት የት ድረስ መሆኑን የገለጹት፡፡

የሕግ ባለሙያው ሲቀጥሉ አዲሱ የንብረት ማስመለስ አዋጅ የያዛቸው ድንጋጌዎች፣ ከዚህ ቀደም በነበረው የፀረ ሙስና አዋጅ ላይም የተካተቱ እንደነበር ይጠቁማሉ፡፡

‹‹አንድ ሰው ወይም አንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ከመደበኛ ገቢው በላይ የሆነ ንብረት ካፈራ ሀብቱን ያፈራበትን መንገድ እንዲያረጋግጥ የሚያስገድድ ሕግ ነበር፡፡ አሁን የወጣውን አዲስ አዋጅ ለየት የሚያደርገው ግን ሕጉ በመንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም ሰው ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን መደረጉ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ማረጋገጫ የማይሰጥበት ሀብት ካፈራ ሊወረስ እንደሚችል በአዲሱ አዋጅ ተቀምጧል፡፡ ይህ በውጭ አገሮች በአውሮፓም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች የተደራጀ ወንጀል የሚፈጽሙ አካላትን ለመቆጠጠር ሥራ ላይ የሚውል ዓይነት ሕግ ነው፡፡ ሕጉ ከዕሳቤ አንፃር ችግር ላይኖርበት ይችላል፡፡ ሆኖም ሕጎች ተፈጻሚነት ባጡበትና ተቋማቱ ልፍስፍስ በሆኑበት በአሁኑ የአገራችን ሁኔታ በሥራ ላይ የመዋሉ ጉዳይ ችግር ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

እሳቸው በግላቸው ከዚህ ቀደም በወጣው የፀረ ሙስና አዋጅ ተጠያቂ የሆነ ሰው እንደማያውቁ ጠቅሰዋል፡፡ ንብረቱ የተወረሰበት ቀርቶ ያፈራውን ሀብት ከየት እንዳመጣ እንዲያረጋግጥ ሲጠየቅ የታዘቡት ሰው አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የፍትሕ ተቋማቱም ሆነ መንግሥት የሕግ ተጠያቂነት ልል በሆነበት አገር ሕጉ ዜጎች ላይ በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ያደረገ ጉዳት ሊያደርስባቸው ይችላል፡፡ ከፍትሕ ሚኒስትሩ ጀምሮ፣ ዳኛ፣ ዓቃቤ ሕግም ሆነ ፖሊስ ከመንግሥት ተፅዕኖ ነፃ የወጡ ናቸው ተብሎ አይታመንም፡፡ በዚህ የተነሳ ነው እንግዲህ አዲሱ ሕግ አደገኛ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚታመነው፤›› በማለትም አደም (ዶ/ር) ሕጉ ሊፈጥር ስለሚችለው ችግር የገለጹት፡፡

አዲሱ አዋጅ ከመንግሥትና ሕዝባዊ ድርጅቶች ሠራተኞች ውጪ ባሉ ማንኛውም ሰው ላይ ተፈጻሚ መሆኑ በአዋጁ ተቀምጧል፡፡ በአገሪቱ ግዛት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከአገሪቱ ግዛት ውጪ የተፈጸሙ ወንጀሎችን እንደሚመለከትም ሠፍሯል፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሐሰተኛ የኦዲት ሪፖርት፣ ሐሰተኛ ዲክራላሲዮን፣ ሐሰተኛ የገቢና ወጪ እንዲሁም የታክስ ሪፖርትና ሌሎችም ሐሰተኛ ሰነዶችን ማቅረብ እንደሚያስጠይቅ ተመላክቷል፡፡

ከዚህ ጋር በማያያዝ ደግሞ ከውጭ የተላከ ገንዘብ አለኝ የሚል ማንኛውም ሰው ገንዘቡ በሕጋዊ የባንክ ሥርዓት ውስጥ ማለፉን የሚያረጋግጥ ተገቢ የባንክ ደረሰኝ ማቅረብ እንደሚኖርበትም አስፍሯል፡፡

አዋጁ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን የመውረስ ድንጋጌው እስከ አሥር ዓመታት ወደኋላ ተመልሶ ተፈጻሚ እንደሚሆን ይገልጻል፡፡ አገሪቱ ወንጀለኞችን ለመክሰስና በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ያለባትን የሰው ኃይል፣ የፋይናንስና የቁሳቁስ አቅም ውስንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሕጉ ወደኋላ ተመልሶ ተፈጻሚ ሲደረግ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ በሕገወጥ መንገድ ያፈሩ ተጠርጣሪዎች ላይ ብቻ እንዲተገበር መደረጉም በረቂቁ ላይ ተብራርቷል፡፡

ሕጉ ከዚህ በተጨማሪም የዲጂታል ገንዘቦችን በተለይም ቢት ኮይን፣ ኤሴሪየም፣ ቴዘር፣ ባይናንስ የመሳሰሉ ኤሌክትሮኒክ መገበያያዎችን በስም በመጥቀስ ጭምር በእነዚህ ላይም የተፈጻሚነት ወሰን እንዳለው ያመለክታል፡፡

አዋጁ ማንኛውም ሰው በይዞታው ሥር ስለሚገኝ ንብረት መረጃ ሲጠየቅ መረጃ በማቅረብ የመተባበር ግዴታ አለበት ይላል፡፡ ይህን ያላደረገ ግለሰብ የአንድ ዓመት እስራትና እስከ 3,000 ብር መቀጮ እንደሚጠብቀው ይገልጻል፡፡ ይህ ቅጣት ግን አሁን አገሪቱ ከምትገኝበት ሁኔታ ጋር እጅግ የሚያንስ በመሆኑ ያልተባበረ ሰው ከበድ ያለ ቅጣት እንደሚጠብቀው ይገልጻል፡፡

አዋጁ ንብረት የማገድና የመያዝ ዕርምጃ ስለሚወስድበት አግባብ ሲያብራራ፣ የንብረት ማገድ ወይም መያዝ ማመልከቻ የሚቀርበው የንብረት መውረስ ሊያስከትል የሚችል ምርመራ እየተካሄደ ከሆነ፣ ክስ ከቀረበ ወይም በተጠርጣሪው ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተላለፈ እንደሆነ ይዘረዝራል፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ በቂ ምክንያት ሲገኝም ንብረት የማገድና የመውረስ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ያክላል፡፡

አዋጁ በመርህ ደረጃ የዕግድ ዕርምጃ በፍርድ ቤት እንደሚተላለፍ ያመለክታል፡፡ በዚህኛው አዋጅ ግን የተጠረጠረው ንብረት በቶሎ የሚሸሽ መሆኑ ከታመነበትና የወንጀል ድርጊቱ ሌላ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ከታመነበት፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ወይም እሳቸው የሚወክሉት የሥራ ኃላፊ በልዩ ሁኔታ የማገድ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ደንግጓል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የሕግ ባለሙያው አቶ መሱድ ገበየሁ በበኩላቸው፣ ሕጉን እስከ ዛሬ ከነበሩ የሙስና ወንጀል አዋጆች የተለየ ሆኖ እንዳላገኙት ገልጸዋል፡፡

‹‹ሙስና ሲባል ሥልጣንን ያለ አግባብ በመገልገል ለራስ ጥቅም ማዋል ሊሆን ይችላል፡፡ ሙስና ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥትን ወይም የሕዝብን ሀብትና ንብረት ለራስ መገልገልም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህኛው አዋጅ ግን ባለሥልጣናትን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ግለሰቦች በሕገወጥ ሀብት ማፍራት ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ግለሰቦች የሕዝብ ወይም የመንግሥት ንብረት ሳይነኩም በሌላ በኩል የአገር ጥቅም ሳይጎዱም ከገቢያቸው ውጪ በሆነ መንገድ ሀብት ካፈሩ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ በሙስና ወንጀል ጊዜ ተጠያቂ የሚሆነው ሙስና ፈጻሚው ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህኛው አዋጅ ግን የሀብቱ ምንጭ የሆነው ብቻ ሳይሆን ሀብቱን ሲገለገልበት የተገኘው ዜጋም ጭምር ነው ተጠያቂ የሚደረገው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በሙስና ወንጀል አዋጁ 881/2007 ላይ እንደተቀመጠው በሙስና የሚጠረጠሩ ሰዎች ሀብት የማካበት ተጠያቂነት ወሰን ከሙስና ፈጻሚው አልፎ፣ በዙሪያው ያሉ የቅርብ ሰዎችና ዘመዶች ሀብት ድረስ ሊሄድ እንደሚችል መደንገጉን የሕግ ባለሙያው ያስታውሳሉ፡፡ የአሁኑ አዋጅ ደግሞ ይህን የተጠያቂነት ወሰን አስፍቶ ግለሰቦች ከመደበኛ ገቢያቸው ጋር በማይመጣጠን ሁኔታ ያፈሩት ሀብትን ጭምር ያካተተ መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡

በዓረብ አገሮች ለፍተው ሀብት ያፈሩ፣ በውጭ አገሮች ተንከራተው ንብረት ያካበቱ ሰዎች ሊወረስባቸው ነው በሚል የሚናፈሰውን ወሬ እንደሰሙ የሚጠቁሙት የሕግ ባለሙያው አቶ መሱድ፣ በአጭር ጊዜ እንዲህ ነው ብሎ አስተያየት ከመስጠት ይልቅ መጀመሪያ ሕጉን በዝርዝር ማጥናት እንደሚመርጡ አስረድተዋል፡፡ ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉም ሕጉ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ይመራል መባሉ ጥያቄ እንደፈጠረባቸው አመልክተዋል፡፡

‹‹በፍትሐብሔር ይመራ ከተባለ አንድ ደሃ ከመንግሥት ጋር ተደራድሮ 50+1 ሚዛን የሚደፋ መከራከሪያ ካቀረበ ንብረቱን ይውሰድ ማለት ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ ይህ አቅም ያለውን መንግሥት የሚጠቅም ነው፡፡ ሰውየው በወንጀል የተጠረጠረ ከሆነ ንብረቱ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓቱ ቢመራ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ከዚያ ውጪ የንብረት ማስመለስ ክሶችን ሁሉ በፍትሐ ብሔሩ እንዳኝ ማለቱ፣ የዜጎችን መሠረታዊ ሀብት የማፍራት መብት ሁሉ የሚቃረን ይመስለኛል፤›› ነው ያሉት፡፡

ሌላው የሕግ ባለሙያ አደም (ዶ/ር) የሕጉ ችግር ሳይሆን፣ የተቋማት አቅመ ቢስነት በኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ ሁሌም ቢሆን ባለሥልጣናት ከተቋማት በላይ በሆኑበትና ልል የሕግ ሥርዓት ባለበት አገር ሕግ ማጥቂያ መሣሪያ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት የተደራጁ ወንጀሎችን መቆጣጠር እንዳለበት፣ ሕገወጥ የምንዛሪ ግብይትን ጨምሮ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን መቆጣጠር እንዳለበት ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚደረገው ለራሱ ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ለአገር ኢኮኖሚና ደኅንነት ሲባል መሆኑን አክለዋል፡፡

‹‹ይህም ቢሆን ግን ተቋማት አቅመ ቢስ በሆኑበትና የሕግ የበላይነት ሥርዓት ባልተረጋገጠበት አገር፣ እንዲህ ያለ ጠንካራ አዋጅ ማርቀቁ ሰዎች ያለ ጥፋታቸው ንብረታቸው እንዲወረስ ሊያደርግ የሚችል ነው፤›› በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ንብረት ባይወረስባቸው እንኳን እንዲህ ባለው ሕግ የተነሳ ሰዎች በሚደርስባቸው ማስፈራራትና ዛቻ ለመሸማቀቅ እንደሚዳረጉ ነው ያመለከቱት፡፡  

ረቂቅ አዋጁ በዩቲዩብ፣ በቲክቶክና በሌሎችም የማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የሚገኝ ገንዘብን ያካት ወይም አያካትት እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም፡፡

People are also reading