Home Back

በአሜሪካ በተካሄደ የሮቦቲክስ ውድድር የኢትዮጵያውያን አሸነፉ

dw.com 2024/10/5
በአሜሪካ በተካሄደው የሮቦቲክስ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ አዳጊ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች በማሸነፍ ሽልማት አግኝተዋል።
በአሜሪካ በተካሄደው የሮቦቲክስ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ አዳጊ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች በማሸነፍ ሽልማት አግኝተዋል።

በአሜሪካ በተካሄደ የሮቦቲክስ ውድድር የኢትዮጵያውያን አሸነፉ

በቅርቡ በአሜሪካን ሀገር  ሚችጋን ግዛት የሎውረንስ ቴክኖሎጂካል ዩኒቨርስቲ ባዘጋጄው ዓመታዊ የሮቦቲክስ ውድድር  ተሳታፊ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተለያዩ ዘርፎች አሸናፊ ሆነዋል።  
የተሳታፊ ቡድኑ መሪ እና አሰልጣኝ እንዲሁም የአቦጊዳ ሮቦቲክስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል መሥራች እና ዳይሬክተር የኢንጅነር ምህረት ዋልጋ እንደምትገልፀው፤ ተማሪዎቹ ላለፉት ሁለት ዓመታት እርሷ በምትመራው  የቴክኖሎጂ ማዕከል ውስጥ ሥልጠና ወስደዋል።በስልጠናው ወቅትም የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን  አቅርበዋል።«ሮቦ ፌስት»በተባለው በዘንድሮው የሎውረንስ ቴክኖሎጂካል ዩኒቨርስቲ ውድድርም እነዚህን የፈጠራ ስራዎቻቸውን ለዕይታ አብቅተዋል።
ከጎርጎሪያኑ ግንቦት 9 ቀን እስከ ግንቦት 12 ቀን 2024 ዓ/ም  በሎረንስ ቴክኖሎጅካል ዩንቨርሲቲ የተካሄደው ይህ ውድድር 16 ዘርፎች የነበሩት ሲሆን ኢንጅነር ምህረት እንደምትለው ኢትዮጵያውያኑ በ5 ዘርፎች ተሳትፈዋል።

ተማሪዎቹ በውድድሩ የተሳተፉት  በሁለት ምድብ ተከፍለው ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምድብ ከ9 እስከ 11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የሰባተኛ እና የስምንተኛ ክፍል  ተማሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን፤ ሁለተኛው ምድብ ደግሞ ከ10ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያሉ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የተሳተፉበት ነው።ከዚህ አንጻር የተወዳደሩበት ዘርፍ እንደየምድባቸው የተለያየ ነው።

በዚህ ሁኔታ  አዳጊ ወጣቶቹ በአቦጊዳ የቴክኖሎጂ ማዕከል  የቀሰሙትን ትምህርት ተጠቅመው ችግር ፈቺ የሆኑ ፈጠራዎችን በማቅረብ፤ ከተወዳደሩባቸው አምስት ዘርፎች መካከልም ሮቦ ፓሪድ፣ ሲኔየር እና ጁኔር ኤግዚቪሽን በተሰኙት ሦስት ዘርፎች በማሸነፍ ተሸላሚ ሆነዋል።በሁለት የውድድር ዘርፎች ደግሞ የስድተኛ እና ስምንተኝነት  ደረጃን አግኝተዋል።

ተማሪዎቹ በውድድሩ ካሸነፉበት የፈጠራ ስራ መካከል ሙቀት እና ቅዝቃዜን እንደአየር ሁኔታው የሚያስተካክል ጃኬት አንዱ ነው።ይህንን ጃኬት የሰሩት በመጀመሪያው ምድብ የሚገኙት የሰባተኛ እና የስምንተኛ ክፍል  ተማሪዎች ናቸው።በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሜካኒካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ውስጥ መምህርት የሆነችው እና ከቡድኑ ጋር ወደ አሜሪካ የተጓዘችው ምህረት ፤ተማሪዎቹ ፈጠራውን የሰሩት በአካባቢያቸው ከሚገኙ ቅሳቁሶች ሲሆን፤ መነሻቸውም በአካባቢያቸው የተመለከቱት ችግር  መሆኑን ታስረዳለች።ራዳርን ጨምሮ 17 ፈጠራዎችን ያበረከተው የ18 ዓመቱ አዳጊ

ችግሩን በዚህ መንገድ ከተገነዘቡ በኋላ ይህንን ችግር በምን መንገድ እንፈታለን የሚለውን ሲሰላስሉ መፍትሄ ሆኖ ያገኙት ሙቀት እና ቅዝቃዜን የሚያመጣጥን ጃኬት መስራትን ነው።ከመስራታቸው በፊት ግን በዓለም ላይ ከዚህ በፊት  የተሰራ መሰል ቴክኖሎጂ ስለመኖሩ ጥናት አድርገዋል።

ይህ የተማሪዎቹ የፈጠራ ስራ በ«ፕሮቶ ታይፕ» ደረጃ  ያለ ነው።የምትለው ምህረት የገንዘብ ድጋፍ ከተገኘ በቀላሉ ወደ ምርት እና አገልግሎት መቀየር  ይቻላል።ያ ከሆነ ይህ ስማርት ጃኬት በተለዋዋጭ አየር ሁኔታ ለሚሰሩ እና ታመው አልጋ ላይ ለዋሉ ሰዎች የሙቀት መጠንን ለማስተካከል እንደሚያግዝ ገልፃለች። ከዚህ  በተጨማሪ፤በሁለተኛው ምድብ የሚገኙት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም ወደ ከባቢ አየር የሚገቡ በካይ ጋዞችን ለመቀነስ የሚያግዝ ንድፈ ሀሳብ እና በፋብሪካዎች ውስጥ የሚነሳ እሳትን ለማጥፋት የሚያግዝ ሮቦት በመስራትም በአሜሪካው ውድድር አሸናፊ መሆናቸውን ከቡድኑ አባላት መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ታነጌታ ተሾመ ይገልፃል።የ16 ዓመቱ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ወጣት ታነጌታ  እንደሚለው ለፈጠራው መነሻ የሆናቸው በዓለም ላይ የሚታየው የአየር የሙቀት መጠን መጨመር ነው።

ወጣቱ እንደሚለው ተማሪዎቹ የሰሩት ሮቦት ጭስን በቀላሉ መለየት ከሚችሉ መሳርያዎች ተያይዞ በፋብሪካዎች ውስጥ የሚቀመጥ ሲሆን፤ ጭስ በሚፈጠርበት ጊዜ መሳርያዎቹ  በቀላሉ ለሮቦቱ መልዕክት እንዲያስተላልፉ ሆኖ የተሰራ ነው። በዚህ መንገድ  ሮቦቱ  መልዕክት ሲደርሰው  በቀጥታ የእሳት አደጋው ወደ ተፈጠረበት ቦታ በመሄድ እሳቱን  ያጠፋል።እሳቱ  ጨርሶ ሲጠፋም ጭስ የሚለየው መሳርያ ምልክት መስጠቱን ያቆማል።
ይህ የሎውረንስ ቴክኖሎጂካል ዩኒቨርስቲ ውድድር  ከ33 ሀገራት የመጡ በርካታ ወጣቶች የተሳተፉበት በመሆኑ፤ ወጣቱ  እንደሚለው ሌሎች ሀገራት በቴክኖሎጂ ዘርፍ የደረሱበትን ደረጃ ለማየት እና ልምድ ለመቅሰም  ረድቷቸዋል። የበለጠ እንዲሰሩም  መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል።ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ዘመኑ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ እድገት ጋር እኩል እንድንራመድ  ሊሰራ ይገባል ይላል።በፈጠራ ስራዎቹ ወደ ቢሊነርነት እያመራ ያለው ወጣት ኢዘዲን ካሚል

እንደ ኢንጅነር ምህረት ገለፃ ፤አሸናፊዎቹ  በውድድሩ ካገኙት የሜዳልያ ሽልማት በተጨማሪ፤ የተወሰኑ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው መማር የሚያስችላቸውን ነፃ የትምህርት ዕድልም አግኝተዋል። በውድድሩ ከሌሎች ሀገራት የመጡት ተወዳዳሪዎች  የተሻለ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀማቸውን የምትገልፀው ምህረት፤ ኢትዮጵያውያኑ ከእነርሱ ጋር ተወዳድረው ማሸነፋቸው ብቻ ሳይሆን መሳተፋቸው በራሱ ለወደፊቱ የበለጠ እንዲሰሩ ብርታት የሚሰጥ ነው ትላለች።

በፈጠራ ስራዎቹ 23 ተማሪዎች በቡድን የተሳተፉ ቢሆንም፤ በገንዘብ ችግር  በአሜሪካ ውድድሩን የተካፈሉት ግን ዘጠኝ ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን ገልፃለች። ከ5 ዓመት በፊት የተመሰረተው አቡጊዳ ሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ ማዕከል ከዚህ በፊትም ሌሎች በማዕከሉ የሰለጥኑ ተማሪዎችን በመሰል ውድድሮች እንዲሳተፉ ማድረጉን ገልፃለች።ማዕከሉ ስልጠናውን በአብዛኛው በነፃ የሚሰጥ በመሆኑ ግን የበለጠ ለመስራት የገንዘብ ችግር እንዳለበት ተናግራለች።
በአሜሪካ ለተካሄደው ውድድር አብርሆት የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ለተማሪዎቹ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረጉ ምስጋና የምትችረው ምህረት፤መንግስት እና የተለያዩ አካላት ፤ለእንደዚህ አይነት የቴክኖሎጂ ስልጠናዎች የበለጠ ድጋፍ ቢያደርጉ በዓለም አቀፍ ደረጃ  ሀገር የሚያስጠሩ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚቻልም አብራርታለች።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ

People are also reading