Home Back

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው]

ethiopianreporter.com 2024/7/6
  • እኔ ምልህ?
  • እ… አንቺ የምትይው?
  • አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ?
  • አዎ፡፡
  • የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም?
  • ምኑ ነው የሚያስገርመው?
  • ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ እንዴት እንደዚያ ዓይነት መልዕክት ያስተላልፋሉ?
  • ምን አሉ? ተገቢ ያልሆነ መልዕክት አስተላልፈዋል እንዴ?
  • ንግግሩን አድምጫለሁ ስትል አልነበር እንዴ?
  • እሱማ አድምጫለሁ።
  • ታዲያ መልዕክቱን እንዴት አልሰማህም?
  • ሰምቻለሁ ግን እንደ አንቺ የተለየ ትርጉም አላገኘሁበትም። ይልቅ ለምን ያሉትን አትነግሪኝም?
  • የምክክሩን ውጤት መንግሥት መቶ በመቶ ይቀበላል አሉ።
  • ታዲያ ይህን ማለታቸው ጥሩ አይደለም እንዴ?
  • እጅግ ትልቅ ነገር ነው እንጂ፡፡
  • እና?
  • እኔም ይህን ሰምቼ እውነትም ቁርጠኛ ሆነዋል ብዬ ሳልጨርስ ሌላ ነገር ተናገሩ።
  • ምን አሉ?
  • ከዚህ በኋላ የሸግግር መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ አይኖርም እንዳታስቡት ብለው እርፍ፡፡
  • ታዲያ እንደዚያ ማለታቸው ምን ያስገርማል?
  • በምክክሩ የሚሳተፉ የሕዝብ ተወካዮች ተወያይተው ስምምነት የሚደርሱበት አንዱ ጉዳይ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚል ቢሆንስ?
  • እህ… በዚህ መልኩ አላየሁትም ነበር።
  • እንዴት?
  • የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚል ሐሳብ ከምክክር ሒደቱ ሊመጣ ይችላል ብዬ አላሳብኩም ነበር።
  • አንተ ከምክክር ሒደቱ የሚገኘው ውጤት ምን ሊሆን ይቻላል ብለህ ነው የምታስበው?
  • ማ… እኔ?
  • እ…?
  • ለምሳሌ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ፕሬዚዳንታዊ ይሁን የሚል ሐሳብ ሊቀርብ ይችላል።
  • እሺ …ሌላስ?
  • ሌላ… የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔር እንዳይደራጁ በሕግ ይከልከል የሚል ሐሳብ ሊቀርብ ይችላል።
  • እሺ ሌላስ?
  • ሰንደቅ ዓላማውና ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል ሊባል ይችላል።
  • ቆይ ግን ምክክሩ የሚካሄደው ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ሐሳብ ለማቅረብ አይደለም እንዴ?
  • ነው እንጂ፡፡
  • ታዲያ ግልጽና ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ ሲባል የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚል ሐሳብ ቢቀርብ ምንድነው ችግሩ?
  • ችግር የለውም፡፡
  • ችግር ከሌለው ይህንን አማራጭ ዝግ ማድረግ ለምን አስፈለገ?
  • ያው… በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እያለ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ተገቢ ባለመሆኑ እንጂ…
  • እንጂ ምን?
  • ችግር ያለው አይመስለኝም።
  • ይህን ሐሳብ የሚያቀርበውም እኮ ሕዝብ ነው።
  • የትኛው ሕዝብ?
  • በምክክር ሒደቱ የሚሳተፉ የሕዝብ ተወካዮች ናቸዋ?
  • እንደዚያ ከሆነ ችግር የሚኖረው አይመስለኝም።
  • እሱን የምትለው አንተ ብቻ ነህ።
  • እንዴት?
  • አለቃህ የሽግግር መንግሥት የለም ብለው በሩን ዝግ አድርገውታላ? ብቻ የዚህ አገር ነገር ማለቂያ የለውም።
  • እንዴት?
  • በአለቃህ ንግግር ተደንቄ ሳልጨርስ ሌላ አስደናቂ ነገር ከተፍ ይላል።
  • ሌላ ምን መጣ?
  • የሽግግር መንግሥት አይታሰብም መባሉ ተገቢ ነው ወይ? ተብለው የተጠየቁት የምክክር ሒደቱ መሪ የሰጡት ምላሽ ነዋ?
  • እሳቸው ምን ምላሽ ሰጡ?
  • የሽግግር መንግሥት የሚባል ነገር ሊቀርብ አይችልም የተባለው በምክክር ሒደቱ መጨረሻ ላይ አይደለም አሉ።
  • እና መቼ ነው?
  • ይህ ሐሳብ ከምክክር ሒደቱ በፊት መነሳት የለበትም ነው የተባለው።
  • ምን?
  • ይሄን ብቻ መሰለህ እንዴ ያሉት?
  • እና… ሌላ ምን ብለዋል?
  • የምክክር ሒደቱ ሲጠናቀቅ የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ከተደረሰ ለመንግሥት ይቀርባል ብለው ቁጭ።
  • እንደዛ አይሉም።
  • አሉ ስልህ?
  • ያሉትን የሚያደርጉት ከሆነ…
  • እ… የሚያደርጉት ከሆነ ምን?
  • ይበሉ፡፡
  • ጠብቆ ነው ላልቶ?
  • ምኑ? …ሴትዮ ያምሻል!
People are also reading