Home Back

ማሕደረ ዜና፣ የኬንያዎች አመፅ፣ ሩቶ «አዉሮፕላኑ አምልጧቸዉ» ይሆን?

dw.com 6 days ago
የኬንያ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ የተቃዉሞ ሰልፈኞችን ጥያቄ ተቀብለዉ አወዛጋቢዉን የታክስ ጭማሪ ደንብ እንደማያፀድቁ ቃል ገብተዋል

ማሕደረ ዜና፣ የኬንያዎች አመፅ፣ ሩቶ «አዉሮፕላኑ አምልጧቸዉ» ይሆን?

ባለፈዉ ሳምንት በዚሑ ዝግጅት ጠይቀን ነበር።የአፍሪቃ ቀንድን የሚያተራምሰዉ ጦርነት፣ግጭትና የፖለቲካ ቀዉስ በርግጥ ጅቡቲና ኬንያን አልነካ ይሆን አይነት ጥያቄ።ኬንያ ሳምንት አልጠበቀችም። ፈጥና መለስች።የሶማሊያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ የዉስጥ ጠበኞች ወይም ያንዱ-የሌላዉ ጠላቶች የሚደራደሩ፣የሚነታረኩ፣ የሚሳለሉባት ናይሮቢ የጎርፍ ደለል፣እጣቢ ግሳንግሷን በቅጡ ሳታፀደ በአደባባይ ሰልፈኞች ጩኸት፣ በፀጥታ አስከባሪዎች ጢስ-ጠለስ ከሁሉም በላይ በነዋሪዎችዋ ደም ትጎድፍ ያዛች።እንዴት? የዛሬ ዝግጅታች ሌላ ጥያቄ ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
 

ሩቶ እንደ ኬንያዊ-የአፍሪቃዊ መሪ 

እንደ ፖለቲከኛ ብልጣ ብልጥ፣ እንደ ደኸ ልጅ አዛኝ፣ እንደ ኃይማኖታዊ ታጋሽ፣ እንደ ምሑር ምክንያታዊ ደግሞም አንደበተሩቱዑ፣ ማራኪ ደፋርም ናቸዉ።ፕሬዝደንት ዊሊያም ኪፕቺር ሳሞኤል አራፕ ሩቶ።

«በተለይ ወጣቱን የማረኩ መሪ» ይላል ኬንያዊዉ የዶቸ ቬለ የኪሲዋሒሊ አገልግሎት ጋዜጠኛ ብሩስ አማኒ።
«ፕሬዝደንት ሩቶ ሥልጣን ሲይዙ ከቀዳሚዎቻቸዉ ሁሉ ወጣት፣ታታሪ፣አዲስ፣ በተለይ ወጣቱን ማራኪና ትልቅ ተስፋ ሰጪም ሆነዉ ነዉ።»

ከዚያች የስምጥ ሸለቆ ትንሽ መንደር ሳምቡት እንደወጣ የካሌንጂን ነገድ ተወላጅ አካባቢያቸዉን የማይዘነጉ-ግን ፍፁም ኬንያዊ፣ ደግሞም ምሥራቅ አፍሪቃዊ ናቸዉ ወይም ይመስላሉ።
መሥከረም 2022 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን ሲይዙ መጀመሪያ ከተሰነዘረላቸዉ ጥያቄዎች አንዱ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት የሚመለከት ነበር።«ኢትዮጵያ ዉስጥ ምንም ነገር ቢሆን ኬንያን ይነካል» መለሱ ዶክተር ዊሊያም ሩቶ።ብዙም አልቆዩ የቀድሞ አለቃቸዉን በልዩ አደራዳሪነት ሾሙ።

ሌላዉ ጥያቄ?-የሶማሊያን የርስበርስ ግጭት የሚመለከት ነበር።«ሶማሊያ የሠፈረዉ የኬንያ ሠራዊት» እያሉ ቀጠሉ የያኔዉ አዲስ ፕሬዝደንት «ተልዕኮዉን ሲያጠናቅቅ ወደ ሐገሩ ይመለሳል።» አከሉ።የሱዳን ጄኔራሎች ከጦርነት ሲመሰጉ፣ኢትዮጵያና ሶማሊያ ሲወዛገቡ ለማደራደር ከሞከሩ የሐገራት መሪዎች ቀዳሚዉ እሳቸዉ ናቸዉ።ደቡብ ሱዳኖችን አሁንም እያደራደሩ ነዉ።
አፍሪቃዊም ናቸዉ።ለኮንጎን ሰላም በሺሕ የሚቆጠር ጦር ኃይል አዝምተዋል።አፍሪቃም በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ መድረክ ተገቢዉ ሥፍራ እንዲሰጣት ተሟግተዋል።ሩቶ አምና ግንቦት ለፓን አፍሪቃ ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር የአፍሪቃ መሪዎች በተጠሩ ቁጥር ብራስልስ፣ዋሽግተን፣ ሞስኮ ወይም ቤጂንግ እየተግተለተሉ መሔዳቸዉን አቁመዉ በጋራ ማሕበራቸዉ እንዲወከሉ ጠይቀዉ ነበር።
«ሌሎች ከኛ ጋር መነጋገር ሲፈልጉ ከሶስቱ (የአፍሪቃ ሕብረ ተጠሪዎች) ጋር መነጋገር አይፈልጉም።50ዎቻችንም መራሕያነ መንግሥታት ይጋብዛሉ።እና ሥብሰባ እንሔዳለን።እያንዳዱ አንድ ደቂቃ ተኩል እንዲናገር ይፈቀድለታል።50 መራሕያነ መንግስታት ከሚያደርጉት ስብሰባ ምን ዓይነት ዉጤት ትጠብቃላችሁ? ምንም የሚገኝ የለም።ከፎቶ ግራፍ በስተቀር።50ዎቻችንም ይደርድራሉ ፎቶ ያነሳሉ።ምናልባት የራት ግብዣ።ዝናንተ ጥሩ ሰዎች ሆይ! ምግብ እዚሕስ መቼ አጣን።»
 

ሩቶ በምዕራባዉያን ተወደዉ ኬንያን የዘነጉ መሪ 

ዓለም አቀፋዊም ናቸዉ።የተፈጥሮ ሐብት እንዲከበር ከሚድራንድ-ደቡብ አፍሪቃ እስከ ፓሪስ ተከራክረዋል።የአሜሪካኖች ታማኝ፣ የድፍን ምዕራባዉያን ተባባሪ ናቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ጥግ የምትገኘዉን የሐይቲን ሠላም የሚጠብቅ ፖሊስ አዝምተዋል።የየመን ሁቲዎችን ለሚወጋዉ የአሜሪካ ጦር ድጋፍ ሰጥተዋል።ለዚሕ ዉለታቸዉ በ15 ዓመታት ታሪክ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ አፍሪቃዊ እግዳ ተብለዉ ዋሕይወት ሐዉስ ተጋብዘዋል።ኬንያ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሳትሆን ድርጅቱ የኬንያን ጦር እንዲያሰለጥን ተፈቅዶላታል።
ሰዉዬዉ በ20 ወራት ዉስጥ 38 ሐገራትን 60 ጊዜ ጎብኝተዋል።ሐገር-ሕዝባቸዉን ችላ ብለዉ ዓለምን ሲዞሩ፣ከሁሉም በላይ የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ምክርና ግፊት ሰምተዉ ግብር ሲጨምሩ ግን የነበረዉ ሁሉ እንዳልነበር ሆነባቸዉ።

የኬንያ ወጣቶች ቁጣ፣ የሩቶ ማምለጫ ብልሐት

ኬንያዊዉ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር ማቻሪያ ሙኔን እንደሚሉት ተቃዉሞዉ መንግስት የሕዝቡን ፍላጎት መዘንጋቱን የሚያረጋግጥ ነዉ።
«ተቃዉሞዉ፣ መንግስት የሕዝቡን ፍላጎት በመዘንጋቱ ምክንያት የመጣ ነዉ።»

ኬንያዊዉ የዶቸ ቬለ ጋዜጠኛ ብሩስ አማኒ እንደሚለዉ ደግሞ ሩቶ በተለይ ለወጣቱ ብዙ ቃል ገብተዉ ነበር።ከቃል ግን አላለፈም።

«ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ለማድረግ ቃል ገብተዉ ነበር።በተለይ ለወጣቶች ሥራ ለመፍጠር፣ ችግራቸዉን ለመስማትና ለማቃለል ቃል ገብተዉ ነበር።እርግጥ ነዉ ሥልጣን ሲይዙ ባዶ ካዝና መረከባቸዉን አስታዉቀዋል።ቆንጠጥ የሚያደርግ ርምጃ እንደሚወስዱም ተናግረዋል።ይሁንና ወጣቱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንቢኝ ማለት ያዘ።ጥሩ ነገር እየተናገርክ መንግስትና ባለሥልጣናቱ የሚያደርጉት ግን ተቃራኒዉን ነዉ ማለት ጀመረ።» 
እና ያ የደገፈ፣ ያደነቀ፣ በንግግር አቀራረባቸዉ የተማረከዉ፣ ወጣት አመፀባቸዉ።የወጣቱ ቁጣ ናይሮቢ ላይ ይንተከተክ ገባ።
ሰልፈኛዉን ለመበተን ፀጥታ አስከባሪዎች እስካለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ድረስ በወሰዱት የኃይል እርምጃ 30 ሰዎች መገደላቸዉን የኬንያ የጤና ባለሙያዎች ማሕበር አስታዉቋል።ፕሬዝደንት ሩቶ ጥፋታቸዉ ለኬንያዎች ከበቂ በላይ ቢሆንም ብልጥ ናቸዉ።

ኢትዮጵያ ዉስጥ የሕዝብ ጥያቄና ቅሬታ ብልጭ ባለ ቁጥር ከወደ አራት ኪሎ እንደምንሰማዉ ሰልፈኛዉን ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለመናድ፣ የጎዳ ላይ ነዉጠኛ፣ ፀረ ሕዝብ ምንትስ» አላሉም።የኬንያ የገንዘብ አዋጅ 2024 የተባለዉን ረቂቅ እንደማያፀድቁ አስታወቁ።ለሟች ቤተሰቦች ሐዘናቸዉን በይፋ ገለፁም።ሮብ።

«የ2024 የገንዘብ አዋጅን አንቀበልም ያለዉን የኬንያን ሕዝብ ግልፅ መልዕክት በጥሞና አድምጬ፣ ተስማምቻለሁ።ሥለዚሕ የ2024ን የገንዘብ አዋጅ በፊርማዬ አላፀድቅም።አዋጁ በምክር ቤቱ መፅደቁ ጠንካራ ቅሬታ እንዳስከተለ ተገንዝበናል።በሚያሳዝን ሁኔታ የሰዉ ሕይወት ጠፍቷል።ንብረት ወድሟል።ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ተጎድተዋል።ለሞቱት ሰዎች ቤተሰቦች በራሴ፣ እዚሕ በተሰበሰቡት አባላትና በሌሎች ኬንያዉን ሥም ጥልቅ ሐዘኔን አገልፃለሁ።» 

ተቃዉሞ ሰልፉ ግን እንደቀጠለ ነዉ።የሰልፈኛዉ ጥያቄም ከረቂቁ  አዋጅ አልፎ ሙስናን ወደ ማዉገዝ፣ ሩቶን ጨምሮ ሙሰኛ የሚባሉ ባለሥልጣናት ከሥልጣን እንዲነሱ ወደ መጠየቅ ተሸጋግሯል። ብሩስ  እንደሚለዉ የግብር ጭማሪዉ አዋጅ አመፁን አቀጣጠለዉ እንጂ የሕዝቡ ቅሬታ የዋለ ያደረ ነዉ።
   
«ጠለቅ ብለሕ ስታየዉ የግብር አዋጁ ለብዙ ዓመታት ዉስጥዉስጡን ሲብላላ የቆየዉ ቅሬታ ማቀጣጠያ ነዉ።ሰልፈኞቹ ሙስናን በተመለከተ፣ባለሥልጣናትንና መሪዎች ተጠያቂ ሲሆኑ ማየት፣ ጥብቅ እርምጃ ሲወሰድ ማየት ይፈልጋሉ።ለዚሕ ነዉ አደባባይ የወጡት።ግፊት ለማድረግ ነዉ።»

ሰልፉ ትናንትም ቀጥሏል።ትናንት ናይሮቢ አደባባይ የወጡ በመቶ የሚቆጠሩ ሠልፈኞች በኬንያ ፀጥታ አስከባሪዎች የተገደሉ ጓዶቻቸዉን ዘክረዋል።መንግስትን አዉግዘዋልም።ሰልፉ በአብዛኛዉ ሠላማዊ ነበር።ይሁንና ብሩስ እንደሚለዉ የሰልፈኞቹ ጥያቄና የተቃዉሞ ምክንያት አሁን መልኩን ቀይሯል።

«አሁን ደግሞ ወጣቶቹ  የተቃዉሞ ርዕሳቸዉን ቀይረዉ ሁሉንም ነገር ተቆጣጠር ወደሚል ዞረዋል።መጀመሪያ ላይ የምክር ቤቱ እንደራሴዎች ረቂቁን በመቀበላቸዉ መልዕክት ለማስተላለፍ ምክር ቤቱን ተቆጣጠር የሚል ነበር።የትናንቱ ሰልፍ የተገደሉ ሰዎችን ለማስታወስ የተጠራ ነዉ።ይሁንና  አላማዉ  ብዙ ሰዎች ሥራ አጥተዉ ፖለቲከኞች ብዙ ገንዘብ ማከማቸታቸዉን መቃወም ነዉ።»
ኬንያ የአፍሪቃ ቀንድን ትርምስ መቀየጧ ይሆን?

የምሥራቅ አፍሪቃ የሠላም ተምሳሌት፣ የዲሞክራሲ አብነት፣ የምጣኔ ሐብት እድገት ቁንጮ የምትባለዉን ኬንያ ባለፉት ጥቂት አመታት ረሐብ፣ ድርቅ፣ የሥራ ማቆም አድማ ግራ ቀኝ ሲያላጓት ነበር።ጎርፍ በመቶ የሚቆጠር ሕዝቧን ገድሎባታል።መቶ ሺዎችን አፈናቅሏል።በሚሊዮን ዶላር የተገመተ ንብረት ጠራርጎ ወስዷል።
ከ2007/8ቱ የምርጫ ዉጤት ማግስት ግጭት ወዲሕ የሰሞኑን ዓይነት ቀዉስ ግን አጋጥሟት አያዉቅም።መዉጪያ መንገድ ይኖራት ይሆን? ፕሮፌሰር ሙኔኔ  «ተቃዉሞ ሰልፈኞች አሸንፈዋል» ይላሉ።ከእንግዲሕ የሚያስፈልገዉ  «ዉይይት» ነዉ።
«ሰዉን ያስቆጣዉን የገንዘብ አዋጅ፣ ፕሬዝደንቱ ሰርዘዉታል።በዚሕ አግባብ ሰልፈኞቹ አሸንፈዋል።ወደፊት መደረግ ያለበት ዉይይት ነዉ።ፕሬዝደንቱ የተቃዉሞ ሰልፈኞችን ደረት ከማስመታት ይልቅ ለመደራደር ፈቃደኛ ናቸዉ።»

ጋዜጠኛ ብሩስ እንደሚለዉ የተቃዉሞ ሰልፉየጎሳ ወይም የዘር ልዩነት አልተንፀባረቀበትም።የተቃዉሞ ፖለቲከኞች ግፊትም የለበትም።ኬንያዉያን፣ የኬንያን መንግስት በተለይ የገንዘብ አዋጁን፣ሙስኛና ብቃት የለሽ ፖለቲከኞችን ተቃወሙ።በቃ። እርግጥ ነዉ ፕሬዝደንቱ ሕጉን ሠርዘዋል።ለመነጋገርም ፈቃደኛ ናቸዉ።ግን ብሩስ እንደጠቆመዉ ተቃዋሚዉ  «ባለስልጣናቱን አዉሮፕላኑ ጥሏችሁ ሄዷል እያለ ነዉ።
                                  
«ፕሬዝደንቱ አሁን ጊዜዉ የዉይይት ነዉ ብለዋል።ከወጣቶችና ጉዳዩ ይመለከተናል ከሚሉ ወገኖች ሁሉ ለመነጋገር ቃል ገብተዋል።ይሁንና በኦን ላይን የሚሰራጩ መልዕክቶችን አሁን በምንነጋገርበት ወቅት እንኳን ብታይ፣ ተጨማሪ የተቃዉሞ ሰልፎች እየተደራጁ ነዉ።በሚቀጥሉት ቀናት ግፊቱን ለማጠናከር ይፈልጋሉ።አዉሮፕላኑ ጥሎ ሔዷል እያሉ ነዉ።»

ሩቶን በ1992  ከፕሬዝደንት ዳንኤል አራፕ ሞይ ሥርዓት በጣሙን ከፖለቲካ ጋር ያቆራኛቸዉ YK 92 የተባለዉን ማሕበር በሚመሩበት ወቅት ነዉ። ለካኑ የፖለቲካ ፓርቲ በዉጤቱም ለሞይ ድጋፍ የሚሰጠዉን የወጣቶች ማሕበር ሞይ ራሳቸዉ ተጠቅመዉበት ራሳቸዉ ሲያፈርሱት ሩቶ በሞይ ተሾሙ።የፖለቲካ መገለባበጥንም ያኔ ጀመሩ።

የ2007/8ቱ ምርጫ ዉጤት ባስከተለዉ ግጭት ተጠያቂ ሆነዉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተከሰዉም ነበር።በፀሎትም፣ በፖለቲካ ብልጠትም፣ በጉልበትም፣ በምዕራባዉያን ድጋፍም ብለዉ ከመወንጀል አመለጡ።የዘንድሮዉን የወጣቶች ቁጣ የሚያመልጡበት ብልጠት፣ ብልሐትና ብቃት ማግኘት-ማጣታቸዉን ግን በርግጥ ጊዜ ነዉ በያኙ።

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 
 

People are also reading