Home Back

መንግሥት ለሀገራዊ ምክክሩ አስቻይ ኹኔታዎችን እንዲፈጥር ኮሚሽኑ ጠየቀ

voanews.com 4 days ago

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ የ2016 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን፣ ዛሬ ዐርብ፣ ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ፣ መንግሥት ለሀገራዊ ምክክሩ አስቻይ ኹኔታዎችን እንዲፈጥር ጠይቋል፡፡

በስካይ ላይት ሆቴል ለምክር ቤቱ አባላት በቀረበው የኮሚሽኑ ዓመታዊ ሪፖርት፣ በ2016 ዓ.ም. የገጠሙት ተግዳሮቶች እና ቀጣይ የሥራ ዕቅዶቹ ያካተተ ነው፡፡

ሪፖርቱን ያቀረቡት ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርኣያ፣ ኮሚሽኑ የዝግጅት እና ከሁለት ክልሎች ውጭ የተሳታፊዎች ልየታ ምዕራፎችን አከናውኖ፣ አጀንዳን በማሰባሰብ ተግባር ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ግጭቶች መቀጠላቸውና ከተለያዩ አካላት የሚነሡ ቅሬታዎች፣ በኮሚሽኑ ሥራ ላይ ተግዳሮት እየፈጠሩ ነው፤ ብለዋል ፕሮፌሰር መስፍን፡፡ በኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ የሚነሣው ጥያቄ አንዱ መኾኑንና በዚኽም ራሳቸውን ከሒደቱ ያገለሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አንዳንድ አካላት ባሉበት ሥራው መቀጠሉን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

አገራዊ የምክክር ሒደቱ ኹሉንም አካላት እንደሚያሳትፍ ዋና ኮሚሽነሩ አንሥተዋል፡፡ ግጭት ባለባቸው በተለይም በዐማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ሒደቱን ማስቀጠል አዳጋች መኾኑን፣ እንዲሁም አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከአመራሮቻቸው እና ከአባሎቻቸው መታሰርና መሰል ጉዳዮች ጋራ በተገናኘ የሚያነሧቸው ቅሬታዎች ተግዳሮት እየኾኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በትግራይ ክልልም፣ ሒደቱን ለመጀመር እስከ አሁን ይኹንታ እንዳላገኙ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ለማስጀመር ያለመ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋራ ቢደረግም እንዳልቀጠለ አመልክተዋል፡፡ ስለዚኽም፣ መንግሥት አስቻይ ኹኔታዎችን እንዲፈጥር ጠይቀዋል፤ ምክር ቤቱም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የዋና ኮሚሽነሩን ማብራሪያ ተከትሎ፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ተነሥተው ውይይት ተደርጓል፡፡

ከዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ ፓርቲ በመወከል ከዐማራ ክልል የተመረጡት ዶር. ደሳለኝ ጫኔ፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ስላለው ሒደት ጠይቀው፣ ዋና ኮሚሽነሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የትግራይ ክልልን ኹኔታ በሚመለከት ደግሞ አቶ መለሰ መና የተባሉ የምክር ቤቱ አባል ጥያቄ አንሥተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ በትግራይ ክልል እስከ አሁን ሒደቱ ያልተጀመረበትን ምክንያት አስረድተው፣ ለማስጀመር ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በዐማራ ክልልም ሒደቱን ለማስቀጠል፣ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ጨምሮ ተያያዥ ተግባራት እንደሚቀጥሉ ጠቁመው፣ ምክር ቤቱም ኃላፊነቱን ይወጣል፤ ብለዋል አቶ ታገሰ፡፡

ገዢው ፓርቲም፣ በምክክር ሒደቱ የሚሳተፍ አንድ አካል ከመኾን ያለፈ ድርሻ እንደሌለው የተናገሩት አፈ ጉባኤው፣ መንግሥትም የአገራዊ ምክክሩን ውጤት ተቀብሎ እንደሚያስፈጽም አስታውቀዋል፡፡

በዐዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን ያከናወነው አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ፣ በቀጣዮቹ ሳምንታት ደግሞ፣ በአራት ክልሎች ውስጥ በተመሳሳይ ጊዜ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን እንደሚያከናውን ፕሮፌሰር መስፍን አርኣያ ገልጸዋል፡፡

ከምክክሩ ሒደት ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ካገለሉ በኮከስ ስም ከተደራጁ ከ10 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ስድስቱ፣ ከኮሚሽኑ ጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ያነሡት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በአሁኑ ወቅት 50 ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋራ እየሠሩ ነው፤ ብለዋል፡፡

ነፍጥ ያነገቡትን ጨምሮ ኹሉንም አካላት ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ እንደኾነና የተሳታፊዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥም፣ በመንግሥት ሊወሰዱ በሚገባቸው ርምጃዎች ላይ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋራ ኮሚሽኑ በቅርቡ እንደሚነጋገር ዋና ኮሚሽነሩ አመልክተዋል፡፡

People are also reading