Home Back

የወባ በሽታ ስርጭት በምእራብ ወለጋ መስፋፋት

dw.com 2024/7/8
Äthiopien I West Wollega - Gimbi Stadt
ምስል Negassa Dessalegn/DW

የወባ መስፋፋት በምዕራብ ወለጋ

በምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ ውስጥ ወባ በሽታ ስርጭት ከክረምት ወቅት መጀመር ጋር ተያይዞ መባባሱን ነዋሪዎች ዐስታወቁ፡፡ በወረዳው ጅንብላ ቱዋንቢ በተባለ አካባቢ በዚህ ሳምንት አራት ህጻናት በወባ በሽታ መሞታቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በቦታው የህክምና ተቋማት በቅርበት ባለመኖራቸው በርካታ ሰዎች በወባ እየተጎዱ እንደሚገኙ  ገልጸዋል፡፡ የምዕራብ ወለጋ ዞን የጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን ጣሰው እንደተናገሩት በዞኑ የወባ በሽታ ስርጭት መጨመሩን አረጋግጠው ባለፉት 10 ወራት በዞኑ ደረጃ 5 መቶ 19ሺ የሚደርሱ ሰዎች በወባ በሽታ መታመማቸውን  ገልጸዋል፡፡

በቆንዳላ ወረዳ በወባ በሽታ የአራት ህጻናት አልፏል

በምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳለ ወረዳ ጅምብላና ገሚ ጋባ በሚባል ቦታዎች የወባ በሽታ ክረምት መግባቱን ተከትሎ ስርጭት መጨመሩን እና በሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ከአካባቢው ነዋሪዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ወረዳ ከባለፈው ሰኞ እስከ ትናትናው ዕለት አራት ህጻናት በወባ በሽታ ሕይወታቸው ማለፉን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

«በበሽታው ህዝቡ በበጣም እየተጨነቀ ነው፡፡ ህጻናት ደግሞ በወባ በጣም እየተጠቁ ነው፡፡ በሁለት ቀን ልዩነት 3 ሰዎችን ቀብረናል፡፡ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ወባ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡»

ሌላው አንድ ልጃቸው በወባ በሽታ ሕይወቷ ማለፉ የነገሩን ነዋሪም የወባ ስርጭት በአካቢው መባባሱን በመግጽ እሳቸው አሁን በሚገኙበት መንደር በትንሹ 15 ሰዎች በወባ በሽታ ታመው ይገኛሉ፡፡ «ባለፈው ዓርብ ወደ ባምሶ የህክምና ጣቢያ ሄድኩኝ ትናንት 10 ሰዓት ገደማ ከባምሶ እየተመለስኩ ባለውበት ሰዓት ነው ህይወቷ ያለፈው፡፡ በብዛት ህጻናት ናቸው በዚህ በሽታ እየተገዱ የሚገኙት፡፡ ጠቅላላ እዚህ እነ ባለሁበት ቦታ የሚገኝ ሰው ብትመለከተው የታመመው በወባ በሽታነው፡፡»

በምዕራብ ወለጋ ዞን የጤና መምሪያ በበኩሉ በዞኑ የወባ ስርጭት ከዚህ ክረምት መግባት ጋር ተያይዞ መጨመሩን አስታውቋል፡፡ በዞኑ ስር በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ውስጥ ተስፋፍቶ እንደሚገኝ የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን ጣሴው ለዶይቸቬለ ተናግረዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን የተናገሩት አቶ መስፍን በሰው ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የደረሳቸው መረጃ እንደለለ ገልጸዋል፡፡

«የወባ በሽታ ጋር ተያይዞ ከመስከረም 2016 ዓ.ም እስከ አሁን ባለው ጊዜ በዞኑ 22 ወረዳዎች ውስጥ ስርጭቱ ተስፋፍተዋል፡፡ ቤጊና ቆንዳላ ወረዳዎች ደግሞ በወባ የሚታወቁ ወረዳዎች ናቸው፡፡ በዚህ ወር ደግሞ ከዝናብ ጋር በመጣሉ ስርጭቱ በጣም እየጨመረ ነው፡፡ ጤና ጣቢያዎች፣ሆስፒታሎች በአሁኑ ጊዜ በቀን ብዙ ሰዎችን እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ በወባ በሽታ መያዛቸው  የተረጋገጡ በዞን ደረጃ በሳምንት ከ10ሺ እስከ 20ሺ ሰው እየተመዘገበ ነው፡፡»

በምዕራብ ወለጋ ዞን በተለይም ቤጊና ቆንዳላን ወረዳን ጨምሮ በርካታ ወረዳዎች ውስጥ የወባ በሽታ ስርጭት ባለፈው ዓመት በወረርሽኝ መልክ ጨምሮ ቆይቷል፡፡ በሐምሌና ነሐሴ 2015 ዓ.ም በቤጊ ሆስፒታል 30 የሚጠጉ ሰዎች በወባ በሽታ ህይወታቸው ማለፉን በወቅቱ ከሆስታሉ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

ነጋሣ ደሳለኝ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ

People are also reading