Home Back

“የመንግሥት ኀይሎች በዐማራ ክልል የጤና ተቋማት ላይ ከጦር ወንጀል የሚቆጠር ጥቃት አድርሰዋል” - ሂውማን ራይት ዋች

voanews.com 5 days ago
ሂውማን ራይትስ ዋች
ሂውማን ራይትስ ዋች

በዐማራ ክልል፣ በመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች እና በፋኖ ታጣቂ ቡድኖች መካከል በመካሔድ ላይ ባለው ግጭት፣ በጤና ተቋማት እና በሠራተኞቻቸው እንዲሁም በታካሚዎች ላይ፣ “እንደ ጦር ወንጀል የሚቆጠር” ሰፊ ጥቃት መፈጸሙን፣ ዛሬ ረቡዕ ይፋ የኾነው የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት አስታውቋል።

የድርጅቱ የአፍሪካ ምክትል ዲሬክተር ላቲሺያ ባድር፣ “የኢትዮጵያ ኀይሎች አንዳችም ተጠያቂነት በሌለበት ኹኔታ፣ በዐማራ ክልል በጤና ተቋማት እና በጤና ሠራተኞች የጦር ወንጀል በሚባል ደረጃ ጥቃት ፈጽመዋል፤” ሲሉ ከሰዋል። ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ ሂውማን ራይትስ ዋች፣ ዛሬ ረቡዕ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፣ ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ፣ በዐማራ ክልል በሚገኙ ቢያንስ 13 ከተሞች፣ በፌዴራል ኀይሎች እና በፋኖ ታጣቂ ቡድኖች መካከል በቀጠለው ግጭት፣ በሕክምና መስጫ ተቋማት እና በሠራተኞቻቸው፣ እንዲሁም በታካሚዎች እና በመጓጓዣ አገልግሎቶች ላይ፣ በኢትዮጵያ የጸጥታ ኀይሎች እና በመንግሥት በሚደገፉ ሚሊሺያዎች፣ እንደ ጦር ወንጀል የሚቆጠር ጥቃት በስፋት መፈጸሙን አትቷል፡፡

“ወታደር የሚሞት ከኾነ ኃላፊነቱን ትወስዳላችሁ” በሚል ርእስ፣ በ66 ገጾች የተቀናበረው ይኸው የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት፣ ካለፈው ነሐሴ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በኢትዮጵያ የጸጥታ ኀይሎች እና በዐማራ ፋኖ መካከል እየተካሔደ ያለው ግጭት ዋና ገፈት ቀማሾች ሲቪሎች መኾናቸውን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አጋሮች፥ ተጠያቂነት እንዲኖርና በጤና አገልግሎቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም፣ እንዲሁም በአገሪቱ ሰብአዊ መብቶች ያሉበትን ኹኔታ እንዲመረምሩ ጥሪ አድርጓል። “የኢትዮጵያ የፌዴራል ኀይሎች፣ አንዳችም ተጠያቂነት በሌለው የተለመደ በሚመስል ኹኔታ፣ የሲቪሎችን ደኅንነት ችላ በማለት ለሰዎች እጅግ አስፈላጊ የኾነውን የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን አጥቅተዋል፤” ሲሉ፣ የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዲሬክተር ላቲሺያ ባደር መናገራቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

የድርጅቱ የአፍሪካ ምክትል ዲሬክተር ላቲሺያ ባድር፣ በጤና ተቋማት እና በሠራተኞቻቸው፣ እንዲሁም በታካሚዎች ላይ የደረሰው ጥቃት አስደንጋጭ መኾኑን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

“በጣም አስደንጋጭ ነው። የኢትዮጵያ ኀይሎች ቅንጣት ተጠያቂነት በሌለበት ኹኔታ፣ በዐማራ ክልል በጤና ተቋማት እና በጤና ሠራተኞች ላይ፣ የጦር ወንጀል በሚባል ደረጃ ጥቃት ፈጽመዋል። የጤና ሠራተኞችንና ታካሚዎችን በዘፈቀደ መግደላቸውን፣ ማሰራቸውንና ማስፈራራታቸውን ደርሰንበታል፤ የጤና አቅርቦቶችን ዝርፊያ እና ውድመትም ሰንደናል።” ያሉት ላቲሺያ የጤና ተቋማት ስጋት ላይ እንዲወድቁ መደረጋቸውንና በሥራቸውም ውስጥ ጣልቃ እንደተገባ መታወቁንም ገልጸዋል።

አክለውም፣ “ይህም ሁሉ በአንድ ቦታ ብቻ ሳይኾን፣ በመላው የዐማራ ክልል ዞኖች በሚገኙ በ13 ከተሞች ውስጥ የተፈጸመ ነው። ሪፖርቱ ከባድ ወንጀል መፈጸሙን ብቻ ሳይኾን፣ በግጭት ውስጥ ባለው ክልል በሚኖሩና ተገቢውን ትኩረት ባላገኙ ሲቪሎች ላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ተጽእኖ እንደሚኖር ያመላከተ ነው።” ብለዋል።

ግጭቱ ከጀመረበት፣ ካለፈው ዓመት ነሐሴ 2015 እስከ ዘንድሮ ግንቦት 2016 ዓ.ም. ድረስ፣ የሰብአዊ መብቶች ቡድኑ፥ 58 የሚደርሱ የጥቃቱን ሰለባዎች፣ ምስክሮች፣ የሕክምና ባለሞያዎች፣ እንዲሁም የርዳታ ሠራተኞችን በርቀት ማናገሩን በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።

“በኅዳር ወር፣ በደላንታ ወረዳ በወገል ጤና ከተማ፣ ምልክቱ በግልጽ በሚታይ አንድ አምቡላንስ ላይ ተፈጽሟል የተባለውን የድሮን ጥቃት ተከትሎ፥ አራት ሲቪሎች ሲሞቱ፣ አንድ ሰው ደግሞ ክፉኛ ተጎድቷል፤ እጅግ አስፈላጊ የኾኑ የሕክምና አቅርቦቶችም ወድመዋል፤” ብሏል።

የወገል ጤና አጠቃላይ ሆስፒታል ሠራተኞች፣ ተጨማሪ ጥቃት ይፈጸማል፤ በሚል ፍራቻ ውስጥ እንደነበሩና ጥቂት በቀራቸው በጀት የገዙት መድኃኒት በሙሉ፣ በአምቡላንሱ ውስጥ እንዳለ አብሮ መቃጠሉን፣ አንድ ሐኪም መናገራቸውን ሪፖርቱ አስፍሯል።

የመብቶች ድርጅቱ፣ “በመንግሥት እንደተፈጸመ ግልጽ ነው” ያለውን በአምቡላንሱ ላይ የደረሰውን ጥቃት የሚያሳዩ ፎቶዎችንና ቪዲዮችን መመልከቱንና ትክክለኛነቱን ማረጋገጡን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኀይሎች፣ የሆስፒታሎችን ሥራ ለአደጋ ማጋለጣቸውንና ማስተጓጎላቸውን፤ የሕክምና ባለሞያዎች፣ የፋኖ ታጣቂ ቡድን ተዋጊዎች እንደኾኑ የሚጠረጠሩትን ጨምሮ፣ ለተጎዱ እና ለታመሙ ሰዎች የሕክምና ርዳታ በማድረጋቸው ምክንያት፣ በወታደሮች ጥቃት እንደደረሰባቸው ሪፖርቱ አመልክቷል።

ወታደሮቹ በተጨማሪም፣ አምቡላንሶችንና ሌሎችንም የሕክምና መጓጓዣዎችን አጥቅተዋል፤ በሰብአዊ ርዳታ ላይ ጣልቃ ገብተዋል፤ የዐማራ ሕዝብን የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት ነፍገዋል፤ ሲል፣ ሂውማን ራይትስ ዎች በሪፖርቱ አስፍሯል።

ባለፈው ጥር ወር፣ ወታደሮች፣ አንድ የሕክምና ባለሞያን ለበርካታ ቀናት አግተው እንደነበርና ሐኪሙም፥ “የመረመረኝ ኮሎኔል፥ ‘አንተ የፋኖ ዶክተር ነህ' ብሎ ጠርቶኛል፤” ሲል ማስታወቁን፤ “ለምን ፋኖን ታክማለህ፤ ፋኖዎች ሰዎች አይደሉም፤ ጭራቆች ናቸው፤” ሲልም ኮሎኔሉ ለሐኪሙ ጨምሮ እንደተናገረው በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።

የፌዴራል ኀይሎች፣ ታካሚዎች ወደ ሕክምና መስጫ ቦታዎች መድረስ እንዳይቻሉ ማድረጋቸውን፤ ታካሚዎችንም ‘ፋኖዎች ሊኾኑ ይችላሉ’ በሚል ጥርጣሬ ብቻ እንደያዙ፤ ይህም የሕክምና ርዳታ በሚሹት ዘንድ ፍርሃትን እንዳሰፈነ ሪፖርቱ ጠቁሟል።

“ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ” ወይም “የጦርነት ሕግ” በሚል የሚታወቀው ሕግ፣ በሲቪሎች እና የሲቪል በኾኑ ነገሮች ላይ ጥቃትን እንደሚከለክል ያስታወሰው የመብቶች ተሟጋች ቡድኑ ሪፖርት፥ የሕክምና ተቋማት፣ የሕክምና ባለሞያዎች፣ ታካሚዎች እና አምቡላንሶች፣ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እንደሚደነግግ አስገንዝቧል።

የኦክሲጂን፣ የመድኃኒት እና የኤሌክትሪክ አለመኖር፣ አስቸጋሪ ኹኔታ እንደፈጠረባቸው ሐኪሞች መናገራቸውን፤ የደም ባንኩ፥ ደምን መሰብሰብ ማቆሙን፤ ለወሊድ የመጣችን ነፍሰ ጡር አገልግሎት ለመስጠት፣ ለጄኔሬተር የሚኾን 20 ሊትር ነዳጅ ይዛ እንድትመጣ ለመጠየቅ ሐኪሞች መገደዳቸውን ሪፖርቱ አካቷል።

በሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ያጋጠመውን ክፍተት ለመሙላት የሚሠሩ የሰብአዊ ርዳታ ድርጅቶች፣ በቀጠለው ግጭት ሳቢያ፣ ካለፈው ነሐሴ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራቸውን ለማከናወን ችግር እንደገጠማቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል። በዐማራ ክልል፣ በትጥቅ የተደገፈው ግጭት ከጀመረ ወዲህ፣ ዘጠኝ የርዳታ ሠራተኞች መገደላቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ አራቱ፣ ካለፈው ጥር ወር ወዲህ እንደተገደሉ በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል።

የርዳታ ሠራተኞች ገጥሟቸዋል ያሏቸውን ችግሮች አስመልክቶ ላቲሺያ ባደር ለአሜሪካ ድምጽ ሲናገሩ፣ “ርግጥ ነው። ግጭቱ እና መንግሥት ኾነ ብሎ በክልሉ የወሰዳቸው ርምጃዎች፣ በዐማራ ክልል በየደረጃው የሚገለጹ ከባድ የሰብአዊ ቀውሶችን አስከትለዋል።” ብለዋል።

አያይዘውም ፣ “በሁለቱም የግጭቱ ተሳታፊዎች፣ በጤና ተቋማት እና በሠራተኞቻቸው ላይ ኾን ተብሎ ጥቃት ተፈጽሟል፤ መንገዶች እና ኬላዎች እየተዘጉ ታካሚዎች መንቀሳቀስ እንዳይችሉ፣ የርዳታ ሠራተኞችም ርዳታን ለሚሹ ወገኖች እንዳይደርሱ ተደርገዋል፤ የርዳታ ሠራተኞች የተገደሉበትም ኹኔታ አለ። ካለፈው ጥር ወዲህ፣ ቢያንስ አራት የርዳታ ሠራተኞች ተገድለዋል። ባለፈው ዓመት፣ እ.አ.አ 2023፣ በግጭቱ ተሳታፊዎች የርዳታ ሠራተኞች ታግተዋል፤ ጥቃትም ደርሶባቸዋል። በአጠቃላይ ኾን ተብሎ የሚወሰደው የኀይል ርምጃ፣ አውዳሚ የኾነ የሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል።” በማለት በወጣው ሪፖርት ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዐማራ ክልል፣ በመንግሥት ኀይሎች እና በፋኖ ታጣቂ ቡድኖች መካከል በመካሔድ ላይ ያለው ግጭት፣ በጤና አገልግሎት ዘርፍ ላይ ሰፊ ውድመት ማስከተሉን፣ የክልላዊ መንግሥቱ የጤና ባለሥልጣናት ባለፈው መጋቢት አስታውቀው እንደነበር ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡ ባለሥልጣናቱ “አክራሪ ኃይሎች” ሲሉ በገለጿቸው ኀይሎች፣ 967 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መውደማቸውን፣ እንዲሁም 124 አምቦላንሶችን መወሰዳቸውን እንዳስታወቁም ሪፖርቱ ጨምሮ አስፍሯል።

በተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ምክር ቤት ቢሮ፣ ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ኀይሎች እና የፋኖ ታጣቂ ቡድኖች፣ በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግጋትን እንደጣሱና በዚኽም፣ ከሁለት ሺሕ በላይ የክልሉ ያልታጠቁ ነዋሪዎች ሰለባ መኾናቸውን ማመልከቱን፣ የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አጋሮች፣ በተለይም የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት፣ በበርካታ መድረኮች፣ በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ፣ ጥልቀት ያለው ዓለም አቀፋዊ ምርመራ እንዲደረግበት ሪፖርቱ አሳስቧል። በዚኽ ጉዳይ ላይ ላቲሺያ ባደር ሲናገሩ፤ “በዐማራ ክልል፣ በጤና ተቋማት እና በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሱትን ጥቃቶች ማውገዛቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። ጥቃቶቹ ከዚህ በፊትም፣ በእ.አ.አ 2019 እና 2020፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎች የተፈጸሙትና እኛም የሰነድናቸው ጥቃቶች አካል መኾናቸውን አጽንዖት መስጠት ያስፈልጋል። የመንግሥት ኀይሎች፣ ኾን ብለው የጤና አገልግሎቶችን ማጥቃታቸው፣ ሕገ ወጥ እና ወንጀል እንደኾነ፣ የኢትዮጵያ አጋሮች ማሳወቅ አለባቸው።” ብለዋል።

በዐማራ ክልል፣ በጤና ተቋማት ላይ የደረሱ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች በግልጽ ሲወገዙ ማየት እንደሚሹ የተቋማቸው ፍላጎት መኾኑን የተናገሩት የድርጅቱ የአፍሪካ ምክትል ዲሬክተር ላቲሺያ “በኢትዮጵያ፣ በተለይም በዐማራ ክልል ያለው ኹኔታ፣ ዓለም አቀፋዊ ምርመራን ይፈልጋል። የርዳታ ድርጅቶች፣ የጤና ሥርዓቱ እንዲያንሰራራ ድጋፍ መጀመራቸውን እናውቃለን። ነገር ግን፣ እንዲህ ዓይነቱ ድጋፍ፣ በገለልተኛ እና ዓለም አቀፍ አካላት ቁጥጥር የሚደረግበት ሊኾን ይገባል፡፡” ብለዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች፣ የምርመራውን ውጤት አስመልክቶ ለኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በጽሑፍ ማስተላለፉን፣ ነገር ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ እንዳላገኘ አስታውቋል።

ላቲሺያም፣ “ኢትዮጵያን በተመለከተ ወትሮም እንደምናደርግው፣ የምርመራችንን ግኝቶች ከበርካታ ጥያቄዎች ጋራ አያይዘን ለመንግሥት ልከናል። እስከ አሁን መልስ አላገኘንም።” ሲሉ አክለዋል።

የአሜሪካ ድምፅ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ በሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ላይ ያላቸውን ምላሽ እና አስተያየት ለማስተናገድ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ለመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ፣ እንዲሁም ለዐማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መንገሻ ፈንታው፣ ስልክ በመደወል እና በጽሑፍ መልእክት፣ አስተያየት እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ወደፊት ምላሻቸውን ካገኘን ይዘን እንቀርባለን።

People are also reading