Home Back

አውሮፕላኖችን በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ውስጥ ማሳረፍ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሊተገበር ነው

ethiopianreporter.com 2024/10/5
spot_img
  • የፕሮጀክቱ በጀት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ብድር እንዲሸፈን ተጠይቋል

ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ውስጥ ማረፍ የማይችሉ አውሮፕላኖችን ማሳረፍ እንዲችሉ ለማድረግ፣ ደረጃውን የጠበቀ ቴክኖሎጂ ሊዘረጋለት ነው። 

ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተቃርበው በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ለማረፍ የሚቸገሩ አውሮፕላኖች ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙ ማረፊያዎች እንዲያመሩ የሚደረግ በመሆኑ፣ ይህ ችግር አውሮፕላኖቹን ለተጨማሪ ወጪና ለተራዘመ የአየር ላይ ቆይታ እየዳረገ መሆኑ ይነገራል። 

ችግሩን ለመቅረፍም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን፣ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ጌታቸው መንግሥቴ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በዓለም ኤርፖርቶች ምድብ አንድ፣ ሁለትና ሦስት የሚባሉ ደረጃዎች እንዳላቸው ገልጸው፣ ደረጃዎቹ የሚወሰኑትም በበርካታ መሥፈርቶች ቢሆንም አንደኛው አየር መንገዶቹ ለበረራ ሒደቶች ውሳኔ መስጠት ይችላሉ ወይ የሚለው መሆኑን አስረድተዋል። 

አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የመጨረሻ ደረጃ ምድብ ሦስት የሚባለው እንደሆነ፣ ይህም አውሮፕላን አብራሪው የአውሮፕላን መንደርደሪያውን ሳይመለከት በአውሮፕላኑ ላይና በሲቪል አቪዬሽን በሚገጠም መሣሪያ የአየር ንብረት ሁኔታውን እንዲመለከት የሚያስችል ነው ብለዋል። 

የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እስካሁን ሲጠቀምበት የነበረው ምድብ አንድ መሆኑን፣ በተለይ የአውሮፕላን መንደርደሪያ ዕይታን የሚከለክል የአየር ሁኔታ ሲኖር አውሮፕላኖቹ ወደ ሌሎች ኤርፖርቶች እንዲሄዱ ይደረግ እንደነበርና አየር መንገዶችም ለከፍተኛ ወጪ እንዲዳረጉና የበረራ ሒደቱም እንዲስተጓጎል ሲያደርግ እንደነበር አቶ ጌታቸው አብራርተዋል። 

ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ለማድረግ በጀቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካይነት በብድር እንዲሸፈን ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ መቅረቡን ገልጸው፣ ምንም እንኳን የተጠየቀው በጀት ባይፀድቅም ሚኒስቴሩ ለጥያቄው ምላሽ መስጠቱን አስረድተዋል። ‹‹ለገንዘብ ሚኒስቴር የቀረበው ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል፣ ሁኔታውን በመረዳት አስፈላጊነቱ ታምኖበታል፤›› ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የሚተገበረው በውጭ ኩባንያ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ በዚህም መሠረት ጨረታ ወጥቶ ኩባንያው መመረጡንና አንዳንድ ሥራዎች ብቻ እንደሚቀሩ ጠቁመዋል፡፡ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ለማድረግ በሚቀጥለው በጀት ዓመት ዕቅድ መያዙንና በዚያው ዓመት እንደሚጠናቀቅ አክለዋል። ፕሮጀክቱ በምን ያህል በጀት ተግባራዊ እንደሚደረግ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወደፊት ሲፀድቅ ይገለጻል ብለዋል፡፡

People are also reading