Home Back

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተባብሶ መቀጠሉን ተመድ አስታወቀ

voanews.com 2024/7/5
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር አርማ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር አርማ
ዋሽንግተን ዲሲ — 

እ.አ.አ. በ2023፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኀይሎች፣ የኤርትራ ወታደሮች፣ ፀረ መንግሥት ታጣቂዎች እና አንዳንድ ያልታወቁ ተዋናዮች በፈጸሙት ጥቃት፣ ቢያንስ 1ሺሕ351 ሲቪሎች መገደላቸውን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

ከተገደሉት ንጹሐን ዜጎች ውስጥ 740 የሚደርሱቱ የሞቱት፣ በአማራ ክልል ውስጥ እንደኾነ ሪፖርቱ አመልክቷል።

እ.አ.አ ከ2023 እስከ 2024 ድረስ፣ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ኹኔታ አስመልክቶ ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኀይሎች፥ ሰው አልባ የአየር ተሽከርካሪዎችን (ድሮኖችን) በመጠቀም፣ ከነሐሴ እስከ ታኅሣሥ ባለው ጊዜ ባካሔዱት የአየር ጥቃት 248 ያልታጠቁ ሰዎች ተገድለዋል፤ ትምህርት ቤቶችንና ሆስፒታሎችን ጨምሮ ጠቃሚ መሠረተ ልማቶችን አውድመዋል፤ ብሏል፡፡ በእነኚኽ ጥቃቶችም የዓለም አቀፍ ሕግጋት መጣሳቸውን በመጥቀስ ስጋት መፈጠሩን አመልክቷል።

የተመድን ሪፖርት አስመልክቶ፣ ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፣ የክልሎቹ ባለሥልጣናት ያወጡት ምንም ዐይነት መግለጫ የለም።

የትግራይ ክልልን መነሻ አድርጎ የተካሔደው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ በትግራይ ክልል ባለው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ መሻሻሎች መታየቱን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ ያም ኾኖ እ.አ.አ በ2023፣ በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ፈታኝ ኾኖ መቀጠሉንና በተለይ በዐማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በዐመፅ እና በግጭቶች ሰብአዊ መብቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።

እ.አ.አ ነሐሴ 4 ቀን 2023፣ በአማራ ክልል የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ተከትሎ በተፈጸመ የዘፈቀደ ርምጃ የመኖር መብትን የመንፈግ፣ በራስ አካል ላይ የማዘዝ መብትን የማሳጣት፣ የዘፈቀደ እስራት እና እገታ፣ ጾታዊ ጥቃት፣ የመሰብሰብ እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብትን መጣስና እንደ አፈና እና በግዳጅ መሰወር የመሳሰሉ የመብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውንም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ሪፖርት ጠቅሷል።

ጥቃቶቹ እና የመብቶች ጥሰቱ በፈንታቸው፣ በተለይ በጥቃቱ የተጎዱትን ጨምሮ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ክፉኛ መጉዳታቸውንም ሪፖርቱ ጨምሮ አመልክቷል።

ከባሕር ዳር አቅራቢያ በምትገኘው መርዓዊ ከተማ፣ በመንግሥት ወታደሮች በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ 89 ንጹሐን ዜጎች መገደላቸውን ያብራራው ሪፖርቱ፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ካለፈው እ.አ.አ 2022 ጋራ ሲነጻጸር በ56 ከመቶ መጨመሩንም ገልጿል።

የተመድን ሪፖርት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአማራ ክልል ተጥሎ የነበረው እና ከሁለት ሳምንት በፊት ያበቃው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አለማራዘማቸው ጥሩ ርምጃ መሆኑን ገልጸው፣ በተገባደደው አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ስም የታሰሩት በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

"ባለሥልጣናቱ በእንቅስቃሴ ላይ የተጣሉትን ገደቦች እንዲያነሡና የሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ መደበኛ የሕግ ማስከበር ሥራዎች እንዲቀጥሉ ጥሪዬን አቀርባለኹ፤" ሲሉ ቱርክ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

ሪፖርቱ፣ አሁንም ግጭት እና ድርቅ፣ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉን እንደቀጠለ እና ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው በሰላም መመለስ አለመቻላቸውን አመልክቶ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ለዜጎች ጥበቃ እንዲደረግና ዘላቂ ሰላምም እንዲሰፍን የተለያዩ አካላት ሊያደርጓቸው የሚገቧቸውን ምክረ ሐሳቦች አካቶ አቅርቧል።

//አድማጮች፣ በዘገባችን ላይ መግለጫው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ዩኤን - ኦቻ) ተብሎ የተነበበው በስሕተት መኾኑን እንገልጻለን።//

People are also reading