Home Back

- Advertisement -

ethiopianreporter.com 2024/10/5

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ ገርጥቶ ከታክሲ መሳፈሪያዎቿ በስተቀር ምልክቷ እየሟሸሸ ነው። በስተምዕራብ በኩል ከተንጣለለው የአፓርታማዎችና የሆቴሎች መንደር በስተቀር የድሮዋ ደማቅ ካዛንቺስ የለችም ማለት ይቻላል። ‹‹ጉድ እኮ ነው እናንተ ሠፈርም እንደ ሰው ያረጃል እንዴ…›› እያለች አንዲት ጠይም ቀጭን ሴት ስትናገር፣ ‹‹አይዞሽ በአዲሱ የኮሪደር ልማት መርሐ ግብር መሠረት ካዛንቺስም በቅርቡ ያልፍላታል…›› ብሎ አንድ ቁመተ ሎጋ ሲመልስላት፣ ‹‹ተው እንጂ፣ ሰው የሌለበት ከተማ ምን ቢያምር ምን ዋጋ አለው…›› እያለ ወያላው ያዳንቃል። አንድ ጎልማሳ ተሳፋሪ ፈገግ እያለ፣ ‹‹እንዳንተ ዓይነቱን ነው መሰል ‹እነሱ ያወራሉ እኛ ግን ሥራችንን እንሠራለን›፣ ‹እኛ ሠርተን ስንጨርስ እነሱ ሰልፊ ይነሳሉ› የተባለው አንተ…›› ሲል የሳቅና የጉርምርምታ ድምፅ ተሰማ፡፡ ወያላው በኩርፊያ ስሜት ሾፌሩን ‹‹ሳበው!›› ብሎ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ደርቢ በሉት!

‹‹እና ‹አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች› ስለኮሪደር ልማቱ ምን አሉ ተባለ?›› ያሽሟጥጣል አንዱ፡፡ ወጣቱ ሾፌር አዲሱን ጨዋታ እየተቀላቀለ፣ ‹‹ዌል እንግዲህ ብዙ ብለዋል ይባላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የመዲናችን ነዋሪ የወሬን እናት የልማት እናት በማሸነፍ፣ እንዲሁም ከሲንጋፖር የተገኘውን ልምድ በመቀመርና ጨከን በማለት ልማቱ መሳለጥ አለበት ብሏል። ሌላዋ እንዲሁ ስሟም መልኳም እንዲጠቀስ ያልፈለገች ወጣት ደግሞ በእውነቱ አንዳንዶች ለልማታችን ያላቸው አመለካከት ‹ፌር› አይመስለኝም። የልማቱ ፋይዳ የሚለካው በተጠቃሚው ሕዝብ ስሜት እንጂ ሩቅ ሆነው በሚታዘቡ መሆን የለበትም ብላለች…›› ሲል ገሚሱ ግራ ተጋብቶ ገሚሱ እየተዝናና ሲያዳምጠው ቆየ፡፡ ድንገት ወያላው፣ ‹‹ከሁሉ ከሁሉ እኔን የገረመኝ ቋንቋችን ራሱ ስደተኛ በሆነበት ዘመን ስደትን አውጋዡ መብዛት ነው…›› ከማለቱ፣ ‹‹ስደት ካማረህ ሂድና የህንድ ውቅያኖስ ዓሳ ነባሪ እራት መሆን ትችላለህ…›› ብሎ ጎልማሳው ሌላ ዙር ሮኬት ሲተኩስበት ፀጥ አለ፡፡ ይገርማል!

ከጉዟችን የተጀመረው ተረብ ቀጥሏል፡፡ ‹‹እዚህ አገር የሰው አፍ እየጠበቁ አላስወራ የሚሉ ተረበኞች በዙ እኮ…›› ብሎ ከጥግ አንዱ አዲስ አጀንዳ ሲያስጀምር፣ ‹‹ወሬ ስለበዛ ልማት ይሻለናል ሲባል ለምን እንማይገባህ እንጃ…›› ብሎ ከአጠገቡ ወዳጁ መለሰለት፡፡ ‹‹ተወው እባክህ፣ ለቲክቶክ የሚሆን ቀልድ ፈልጎ እኮ ነው የሚቀባጥርብን…›› እያለ አንድ ጎረምሳ ቢጤ ከኋላ መቀመጫ ነገር ሲያቀጣጥል፣ ‹‹ቲክቶክ እኮ የሚሊዮኖች እንጀራ መብያ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ እንዳንተ ዓይነቱ ግን እንጀራ ማብሰያው ምጣዱን ትቶ የድስት ማማሰያ እየላሰ ነገር ያደራል…›› ብሎ መለሰለት፡፡ የሁለቱ ተረብ በርቀት የሚካሄድ ቢሆንም፣ ተራርቀው የተቀመጡ ነገረኛ ወዳጆች ሳይሆኑ አይቀርም የሚል ሐሳብ ሽው ያለባቸው አንድ አዛውንት፣ ‹‹እናንተ ናችሁ የገባችሁ ልጆቼ፣ እንዲህ በቀልድ እያዋዛችሁ ሰተት አድርጋችሁ ወጥመዳችሁ ውስጥ ልታስገቡን ታደባላችሁ፡፡ ሌላው ጅል ግን በአፍ ዕላፊ ካልተጋደልን እያለ ለገላጋይ እያስቸገረ እኮ ነው አገር መላ ቅጥ ያጣችው…›› ብለው ሲናገሩ ጎረምሶቹ ተሳሳቁ፡፡ እንዲያ ነው ብልጠት!

በሦስቱ ወጣቶች ምልልስ ዘና ተብሎ ፈገግ ማለት ሲጀመር ሁለት ጎልማሶች ከደጅ ይዘውት የተሳፈሩትን ነገር ጀምረው ኃይለ ቃል መለዋወጥ ጀመሩ፡፡ አንዱ ሌላውን ወቀሳ አይሉት ዘለፋ በሚመስል አነጋገር፣ ‹‹ድሮም እኮ አንተ ቀኝ መንገደኛ ስለሆንክ ተራማጅ አስተሳሰብ አይዋጥልህም…›› ሲለው፣ ‹‹የአንተና የቢጤዎችህ ግራ ዘመምነት ያተረፈልን ብሔርተኝነትን ቀፍቅፎ እርስ በርስ ማፋጀት ነው…›› በማለት መለሰለት፡፡ ‹‹እኛማ ለአገራችን ዕድገትና ህልውና ስንል ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ወደኋላ የማንል፣ ግንባራችንን ለጥይት ደረታችንን ለጦር አሳልፈን የምንሰጥ ቆራጦች መሆናችንን እኮ በተግባር ያረጋገጥን ትውልዶች ነን…›› እያለ ፉከራ ሲቀጣው፣ ‹‹በል… በል… ተወው ወንድሜ አሁንም ያ ዕብደት አልበረደላችሁም ለካ፡፡ እኔ የምለው ከግድያ ታሪክ በስተቀር ምን የሚያስመካ ነገር ኖሮ ነው ይህ ሁሉ ድንፋታ…›› ሲሉ ሳቅ በሳቅ፡፡ ይሳቅ እንጂ!

በአንድ ሁከተኛ የተነሳውን አጀንዳ ለማስረሳትና የተሳፈሪዎችን ቀልብ ለመሳብ ይመስላል ወጣቱ ሾፌር ሬዲዮ ከፍቶ የሰዓቱን ዜናዎች ያስደምጠን ጀመር። ‹‹የቡድን ሰባት አገሮች ዕግድ ከተደረገበት የሩሲያ 300 ቢሊዮን ዶላር ሀብት ወለድ ላይ ለዩክሬን 50 ቢሊዮን ዶላር ብድር ፈቀዱ…›› የሚለው ዜና ሲሰማ፣ ‹‹በአዛኝቱ ማርያም፣ እነዚህ ምዕራባውያን የሚባሉ ጉዶች በቃ የኑክሌር ጦርነት አስጀምረው ዓለም እንድትጠፋ ሊያደርጉ ነው፡፡ ምዕራባውያን አገሮችን የሚመሩት ሰዎች ጭንቅላታቸው አይሠራም እንጂ፣ እንዲህ ዓይነቱ አስደንጋጭ ውሳኔ ለአገሮቻቸው ጭምር ይዞት የሚመጣው ጦስ በእኔ ቢጤው ሳይቀር በቀላሉ የሚታወቅ ነው…›› ብለው አዛውንቱ በንዴት ሲናገሩ፣ ‹‹አይ ፋዘር ማንም ጊዜ የሰጠው ወንበዴ እኮ ነው ዓለማችንን ወደ ገሃነመ እሳት ለመክተት የሚጣደፈው፡፡ እኔ የማይገባኝ እኛ ተራ ሰዎች በቀላሉ የምንረዳውን ቆጡ ላይ ያሉ ሰዎች ለምን መገንዘብ እንደሚያቅታቸው ነው…›› ብላ ያቺ ቀጭን ሴት ስትመልስ፣ ‹‹አንቺ ደግሞ ሁሉንም በአንድ ቅርጫት ከተሽ አንድ ላይ አትመዝኚ…›› የምትለው ቀላ ያለች ወጣት ናት፡፡ የጥቅም ግጭት ይኖር ወይ ያሰኛል!

በኮሪደር ልማት የተጀመረው ወግ የቡድን ሰባት አገሮችንና ሩሲያን አካሎ አራት ኪሎ ደረስን፡፡ የአራት ኪሎ አደባባይ ከአራቱም አቅጣጫዎች በኩል በደረሱ ተሽከርካሪዎች ጭንቅንቅ ብሎ ለትራፊክ ፖሊሶች ጭምር ውክቢያ ፈጥሯል፡፡ የፓርላማው መብራት ታልፎ አደባባዩ ለመድረስ ቢያንስ ሃያ ደቂቃዎች ተቃጥለዋል፡፡ ከአደባባዩ ተወጥቶ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እስኪደረስ ደግሞ ተጨማሪ ደቂቃዎች ነጎዱ፡፡ በዚህ መሀል ነበር፣ ‹‹እናት አገር ኢትዮጵያ… እናት አገር ኢትዮጵያ…›› የሚለው የሙዚቃ ንጉሡ ጥላሁን ገሠሠ ጥዑመ ዜማ ከሬዲዮው ሲለቀቅ፣ ‹‹ይህ ሁሉ መንገላታታችን እኮ ለእናት አገር ኢትዮጵያ እንጂ ለማንም ስላልሆነ፣ በኮሪደር ልማቱ ሳቢያ ለሚደርስ ጊዜያዊ እንግልት መበገር የለብንም…›› እያለ አንዱ ከጋቢና መናገር ሲጀምር፣ ‹‹ለአገር ልማት አይደለም ጊዜን ሕይወታችንን ብንሰጥ ምንም ችግር የለውም… ነገር ግን…›› ብሎ ሌላው ጀምሮ ሲተወው፣ ‹‹አይዞህ ልጄ ተንፍሰው፣ ሁሉም ንግግራችን ለአገር እስከጠቀመ ድረስ ተናገረው፣ ካልረባ ግን ተወው…›› ሲሉ አዛውንት ሳቅ በሳቅ ሆንን፡፡ ወይ ተረብ!

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ‹‹እኔ ደግሞ አንድ ነገር ተናግሮ ነገር ግን… እያሉ ሌላ ነገር መደንጎር ነው የሚያስጠላኝ…›› ይላል ጎልማሳው፡፡ አጠገቡ ያለው ደግሞ፣ ‹‹እኛ እኮ ልማቱን አንጠላም፣ ነገር ግን… የሚሉ አስመሳዮች ናቸው እኮ በቀደም ፒያሳን አጨናንቀው ፎቶ ሲነሱ የነበሩት…›› ብሎ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ሲያመጣ ሰማነው፡፡ ‹‹እናንተ ልጆች ድሮም ሆነ አሁን በአገር ጉዳይ አንድ ተሁኖ አይታወቅም፡፡ ለምሳሌ አገር ስትወረር አንድ ላይ ሆኖ መመከት የምንታወቅበት ታሪካችን ስለሆነ ምስክር አይጠራበትም፡፡ ነገር ግን አገር እንዴት ትመራ፣ ልማቷና ዕድገቷ ምን ይምሰል፣ ምን ዓይነት ሕገ መንግሥት ይኑራት፣ የአካባቢዎች አከላለልና አስተዳደር እንዴት ይሁን፣ ምን ዓይነት ፌዴራላዊ ሥርዓት ይኑረን፣ የንብረትና የመሬት ይዞታውስ፣ የምርጫ ዓይነቱስ እንዴት ቢሆን ይሻላል፣ ወዘተ እየተባለ ክርክሩ አሁንም ድረስ አለ፡፡ አሁን በተያዘው የከተማ ልማት ልዩነቱ በአግባቡ ከተያዘ ለዕድገት ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ የሚጎዳን ግን አጉል ብሽሽቅ ነው፡፡ ብሽሽቁ ነው ወደ ፍጅት የሚወስደን…›› ብለው አዛውንቱ ሲያስረዱን በአንክሮ ሰማናቸው፡፡ ግሩም ነው!

ከአራት ኪሎ ወደ ስድስት ኪሎ በዔሊ ጉዞ እየተንፏቀቅን ስንጓዝ፣ ‹‹ከዛሬ ሰላሳ ዓመት በፊት በዚህ ጎዳና ላይ አንዳንድ ሽው እያሉ ከሚያልፉ የቤት አውቶሞቢሎች በስተቀር መጨናነቅ የሚሉት ነገር አይታወቅም ነበር…›› የሚለው ጎልማሳው ነው፡፡ ‹‹ዕድሜ በከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኘው ኢኮኖሚያችን አገሩ ሁሉ ከናፍጣ እስከ ኤሌክትሪክ መኪኖች አጥለቅልቀውታል…›› ብላ ያቺ ቀይ ወጣት ተናገረች፡፡ ‹‹አይ ልጄ በሠራነው ሳይሆን በገዛነው እየተመፃደቅን ስለኢኮኖሚ ዕድገት ማውራት አይቻልም…›› ሲሉ አዛውንቱ፣ ‹‹እንዴ ፋዘር አልሰሙም እንዴ የመጪው ዓመት በጀታችን ትሪሊዮን ብር ሊደርስ ትንሽ እንደቀረው…›› ከማለቷ፣ ‹‹ሰምቻለሁ ልጄ፣ የትሪሊዮን ብር በጀት ጉድለቱንና የዋጋ ንረቱን ጨምረሽ ከዶላር ምንዛሪ ጋር አንድ ላይ ስትመቺው የመግዛትን ሳይሆን የመሥራትን ሚስጥር ትረጃለሽ…›› አሉ፡፡ ልጅት አሁንም፣ ‹‹ፋዘር ቻይናውያን እኮ የአንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር ጉዞ በአንድ ዕርምጃ ነው የሚጀመረው ይላሉ እኮ…›› ስትላቸው፣ ‹‹አሁን ጥሩ ነገር አመጣሽ፣ የእኛም ሆነ የእነሱ አባባሎች የሚነግሩን ሠርቶ የማደግን ሚስጥር እንጂ፣ ገዝቶ የመመፃደቅን አባዜ አይደለም፡፡ ሚስጥሩ ያለው የሚባሉ ነገሮች ውስጥ ነው…›› በማለት ሲመልሱ ስድስት ኪሎ ደርሰን ‹‹መጨረሻ…›› ተብለን ተሸኘን፡፡ መልካም ጉዞ!

People are also reading