Home Back

የሙቀቱ መጨመር በድሬ ዳዋ በህመምተኞች ላይ ስጋት አሳድሯል

dw.com 2024/7/8
አንድ የከተማዋ ነዋሪ " ከፍ ብሏል" ባሉት የከተማይቱ ሙቀት መጨመር እንደ ደም ግፊት ባሉ በሽታዎች የሚታመሙ ሰዎች "ስጋት ላይ" ናቸው ብለዋል።

በድሬ ዳዋ ከተማ የሙቀት መጨመር ምን ተጽዕኖ አሳደረ ?

በድሬደዋ የሚስተዋለው የሙቀት መጨመር ነዋሪውን ምቾት ሲነሳ እንደ ደም ግፊት ባሉ በሽታዎች ለሚታመሙ ሰዎች ስጋት መፍጠሩን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናገረዋል።

በቁጥር ደረጃ ጉልህ ባይባል እንኳ በአየር ሁኔታው ላይ ለውጥ መኖሩን የሚቲዎሮሎጂ ተቋም አስታውቋል።

በሙቀቱ መጨመር ሳቢያ በአስተዳደሩ የመንግስት ሰራተኞ የስራ ሰዓት መግቢያ እና መውጫ ላይ ማሻሻያ ተደርጓል።

ላለፉት ሶስት እና አራት ሳምንታት በድሬደዋ የሚስተዋለው ወበቃማ የአየር ሁኔታ ለነዋሪዎቿ ምቾት የሚሰጥ አይደለም። ለዶይቼ ቬለ አስተያየት የሰጡ አንድ የከተማዋ ነዋሪ " ከፍ ብሏል" ባሉት የከተማይቱ ሙቀት መጨመር እንደ ደም ግፊት ባሉ በሽታዎች የሚታመሙ ሰዎች "ስጋት ላይ" ናቸው ብለዋል። በመሰል በሽታዎች ሰዎች እየሞቱ ነው ሲባል መስማታቸውን ጠቁመዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪም  ሙቀቱ በጣም እያየለ መምጣቱን ጠቅሰው የልብ ህመም እና ደም ግፊት ባሉ በሽታዎች ለሚታመሙ ሰዎች ይበልጥ ጫና ሳይፈጥር አልቀረም ሲሉ ሀሳባቸውን ገልፀዋል።

በድሬዳዋ ና ሲቲ ክላስተር የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ መላኩ ታከለ በቁጥር ደረጃ ጎልቶ የሚገለፅ ባይሆንም በሙቀት መጨመሩ ላይ ለውጥ መኖሩን ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል።

በአካባቢው ባለፉት ጊዜያት በነበሩ የደመና ክምችቶች ሳቢያ የሚፈጠረው ወበቃማ የአየር ሁኔታ ሰዎች ላይ የመታፈን ስሜት እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።

በነዚህ ጊዜያት  በቀን ጊዜ ረዘም ላሉ ሰዓታት እንቅልፍ አይመከርም የሚል ሀሳብ የሰጡት አቶ መላኩ ከመጪው ሰኔ ወር አጋማሽ አንስቶ የሚመጣው የክረምት ወቅት በመሆኑ አሁን የሚታየው የሙቀት ሁኔታ የመቀነስ ሁኔታ ይኖረዋል ብለዋል።

በድሬደዋ እና አካባቢው ከወትሮ በተለየ የሚስተዋለውን ይህን የሙቀት ሁኔታ መነሻ በማድረግ ወቅቱ እስኪሻሻል ድረስ የድሬደዋ አስተዳደር ካቢኔ በአስተዳደሩ የመንግስት ሰራተኞች የስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ላይ ማሻሻያ የሚያደርግ ውሳኔን ባሳለፍነው ሳምንት አሳልፏል።

መሳይ ተክሉ 

ታምራት ዲንሳ 

ሸዋዬ ለገሰ

People are also reading