Home Back

ገጣሚ እና ኹለገቡ የሥነ ጽሑፍ ሰው ነቢይ መኰንን ዐረፈ

voanews.com 5 days ago
ተወዳጁ ገጣሚ፣ ተርጓሚ፣ ደራሲ እና የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነቢይ መኰንን
ተወዳጁ ገጣሚ፣ ተርጓሚ፣ ደራሲ እና የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነቢይ መኰንን

ተወዳጁ ገጣሚ፣ ተርጓሚ፣ ደራሲ እና የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነቢይ መኰንን፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በሞት መለየቱን፣ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል አስታውቋል፡፡

ባደረበት ሕመም ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ በዛሬው ዕለት ያረፈው ኹለገቡ የሥነ ጽሑፍ ባለሞያው ነቢይ መኰንን፣ ከመሥራቾች አንዱ ኾኖ በዋና አዘጋጅነት በሠራባት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፣ መለያ አሻራዎቹን አሳርፏል።

ባህል እና ጥበብ ለአገራዊ ለውጥ ጽኑ እምነት እንዳለው የሚገልጹት ባልደረቦቹ፣ በልዩነት የሚታወቅባቸውን ሳምንታዊ ርእሰ አንቀጾቹን በተረት እና ምሳሌ ከመጻፍ ጀምሮ፣ ጋዜጣዋ በጥበብ እና ባህል ላይ አተኩራ እንድትሠራ ማድረጉን ይናገራሉ።

ዝነኛው ገጣሚ ነቢይ፣ ተከታታይ የግጥም መድበሎች ጸሐፊ ብቻ አይደለም፡፡ ወጣት ገጣምያንና ጸሐፍት በአዲስ አድማስ ላይ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ሰፊ መድረክ በማመቻቸት፥ ተተኪ ጸሐፍት፣ ደራስያንና ገጣምያን እንዲፈሩም አስችሏል፡፡ ከእነርሱም፣ መጻሕፍትን በማሳተም ለመታወቅ የበቁ ደራስያንና ገጣምያን ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ነቢይ ዝነኛ የቴያትር እና ድራማ ጸሐፊም ነበር፡፡ ከዓመታት በፊት “ባለጉዳይ” የተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ለእይታ አብቅቷል፤ አንጋፋው አርቲስት አበበ ባልቻ፣ ራሱ ነቢይ መኰንንና ሌሎችም አርቲስቶች ተውነውበታል፡፡ በድጋሚም ቀርቦ በከፍተኛ አድናቆት ታይቷል፡፡ “ናትናኤል ጠቢቡ” የተሰኘ ተውኔትም ተርጉሞ ለመድረክ አቅርቧል፡፡ “ጁሊየስ ቄሳር” ሌላው ተርጉሞ ለእይታ ያበቃው ተውኔት ነው፡፡

በመጻሕፈት በኩል፣ “Gone with The Wind” የተሰኘውን የማርጋሬት ሚሼል የአሜሪካ ክላሲክ መጽሐፍ፣ “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ርእስ የተረጎመበት ዳጎስ ያለ መጽሐፉ ተጠቃሽ ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጨረሻ ለኅትመት የበቃው ይኸው መጽሐፉ፣ በደርግ መንግሥት በማዕከላዊ ታስሮ በነበረበት ወቅት በሲጋራ ወረቀት ላይ እየተረጎመ በድብቅ በማስወጣት በመጨረሻ ሲፈታ ያሳተመው ነው፡፡

ሌላው መጽሐፉ፣ ከፍተኛ ተነባቢነትን የተቀዳጀው “የኛ ሰው በአሜሪካ” የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻው ነው፡፡ በአሜሪካ በሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ላይ ያጠነጥናል፡፡ ሦስተኛው መጽሐፉ ደግሞ፣ “የመጨረሻው ንግግር” የተሰኘ ሲኾን፣ “The Last Lecture” ከሚለው መጽሐፍ የተመለሰ ነው፡፡ ሌሎችም ያልታተሙ በርካታ ሥራዎች አሉት፡፡

የሦስቱ መጻሕፍት ምረቃ በቅርቡ በተከናወነበት መድረክ ላይ፣ ኹለገቡ የሥነ ጽሑፍ ሰው ነቢይ መኰንን የሕይወት ታሪኩን ጽፎ እንደጨረሰ ተገልጾ ነበር፡፡

በቀድሞ ናዝሬት በአሁን አጠራር አዳማ ከተማ የተወለደውና የዐፄ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት ፍሬ የኾነው ገጣሚውና ኹለገቡ የሥነ ጽሑፍ ሰው ነቢይ መኰንን፣ በችሎታውም ኾነ በታዋቂነቱ የማይታበይና የማይኮፈስ፣ ይልቁንም ለቀረቡት ኹሉ ደግነቱ እና ቅንነቱ ልዩ እንደነበር፣ ወዳጆቹ እና የሥራ ባልደረቦቹ በከፍተኛ ስሜት ይመሰክሩለታል፡፡

በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አብሮት በመሥራት ጠቃሚ ክህሎት መቅሰሙን የሚናገር ባልደረባው፣ ነቢይ፣ በደርግ ዘመን በኢሕአፓ አባልነቱ ፀረ አብዮተኛ ተብሎ በማዕከላዊ ታስሮ ለ10 ዓመታት መከራውን ቢያይም፣ በእስራቱ ከማማረር ይልቅ፣ “እርሱ እና ዘመነኞቹ በአብዮቱ ወቅት ያሳለፉትን በጎም ኾነ ክፉ ያሁኑ ትውልድ እንዲማርበት ከመጻፍ እና ከመናገር ቦዝኖ አያውቅም፤” ይላል፡፡

“ሐሳብን አይፈራም፡፡ ለሕዝብ እና ለአገር የሚጠቅም አንዳች ሐሳብ ያላቸው ወገኖች ኹሉ፣ እንዲጽፉ ሲያበረታታና ሲደግፍ ኖሯል፤” በማለትም ያክላል፡፡

ነቢይ መኰንን፣ ይኽን የእስር ጊዜውን በተመለከተ ከሸገር ራዲዮ የጨዋታ ፕሮግራም አዘጋጅ መዓዛ ብሩ ጋራ ባደረገው ረዘም ያለ ተከታታይ ቃለ ምልልስ በስፋት አውግቶታል።

People are also reading