Home Back

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ያጋጠመው የነዳጅ እጥረት በበዓል ምክንያት ከጂቡቲ ባለመጫኑ እንደሆነ ተገለጸ

ethiopianreporter.com 2024/10/5
spot_img

በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ሰሞኑን የሚታየው የነዳጅ እጥረት፣ በበዓል ምክንያት ለሁለት ቀናት ከጂቡቲ ነዳጅ ባለመጫኑ እንደሆነ ተነገረ፡፡

የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢዎች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምሕረቱ የነዳጅ እጥረቱ በከተማዋ መከሰቱን ለሪፖርተር አረጋግጠው፣ እጥረቱ ያጋጠመው በዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል ምክንያት እሑድ ሰኔ 9 በማግሥቱ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ነዳጅ ከጂቡቲ ባለመጫኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የነዳጅ ማጓጓዝ ሒደቱ አምስትና ስድስት ቀናት የሚወስድ መሆኑንና አሁን የሚስተዋለው እጥረት በመጪዎቹ ቀናት እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ የነዳጅ ማደያዎች ከሚታየው የነዳጅ እጥረት ባለፈ፣ ማደያዎች ነዳጅን ከተጠቃሚዎች እንደሚደብቁ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች ገልጸዋል፡፡ በድርጅቱ ከተገለጸው ምክንያት በተጨማሪ ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ በውኃ ፕላስቲኮች ጭምር የሚሸጡ መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ባለፉት ሳምንታት በመዲናዋ ነዳጅ ለመቅዳት የሚጠብቁ ረዣዥም የተሽከርካሪ ሠልፎች መታየታቸውንና አሁንም እጥረቱ እንዳለ አክለዋል፡፡

የነዳጅና ኢነርጅ ባለሥልጣን በተለይ ሰው ሠራሽ የነዳጅ እጥረት እንዲኖር በሚያደርጉ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ሲገልጽ ቢደመጥም፣ አሽከርካሪዎች ግን አሁንም ይህ ድርጊት መቀጠሉን ይናገራሉ፡፡ ባለሥልጣኑ የነዳጅ እጥረቱ እንዲፈጠር በሚያደርጉ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ዕርምጃ መውሰድ የሚያስችለውን የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

የሕግ ማዕቀፉ በነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ እያለ እንደሌለ ማስመሰል፣ የነዳጅ ግብይትን በጥሬ ገንዘብ ማከናወን፣ ነዳጅ በተለያዩ ሥፍራዎች ደብቆ ማስቀመጥ፣ በነዳጅ ማደያዎች ከፍተኛ ወረፋ እንዲኖር ማድረግና በነዳጅ ኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ዕርምጃ መውሰድ የሚያስችል መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡ 

በሌላ በኩል ስምንት ያህል የነዳጅ ማደያዎች በከተማዋ እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት መፍረሳቸውን የነዳጅና ኢነርጅ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሔኖስ ወርቁ ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በፈረሱት ማደያዎች ምክንያት አገልግሎት እየሰጡ ባሉ ማደያዎች ላይ ጫና መፍጠሩንም ጠቁመው ነበር፡፡

የፈረሱት ማደያዎች ለበርካታ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር፣ በሥራ ላይ ያሉትም ነዳጅ ለመገልበጥም ሆነ ለተሸከርካሪዎች መስተንግዶ የማይመቹ መሆናቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

People are also reading