Home Back

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

ethiopianreporter.com 3 days ago
  • አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላነጋግርህ የፈለኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እርስዎማ ቀጠሮ መያዝ አያስፈልግዎትም፣ ምን ገጠመዎት?
  • እኔማ ምን ይገጥመኛል አንተኑ ልጠይቅህ እንጂ?
  • ምን?
  • እውነት ለመናገር የማየው ነገር አሳስቦኛል፡፡
  • ይንገሩኝ ምንድነው ያሳሰበዎት?
  • ሌት ተቀን የሚሠራው ነጋዴ እየከሰረ ነው።
  • መቼም የውጭ ኃይሎች የፈጠሩብንን ችግር ያውቁታል።
  • ከእሱ ጋር አይገናኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት?
  • ሌት ተቀን የሚሠራ ታታሪ ነጋዴ ችግር እሱ አይደለም።
  • ምንድነው?
  • ታታሪ ነጋዴ እየመነመነ ሳለ በተቃራኒው ግን ሌላ…
  • በተቃራኒው ምን?
  • መሽቶ ሲነጋ ሀብት አፍርተው የሚታዩ ሰዎች እንደ አሸን እየፈሉ ነው።
  • ምን ማለትዎ ነው?
  • ጠንክሮ መሥራት ሀብት የሚፈጠርበት መንገድ መሆኑ ቀርቶ ሌላ ዓውድ ተፈጥሯል እያልኩ ነው፡፡
  • የምን ዓውድ?
  • ሲነጋ ሀብታም መሆን የሚቻልበት ዓውድ።
  • አልገባኘም?
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ምነው?
  • ሁሉንም ነገር አስረዳ እያሉኝ እኮ ነው፡፡
  • እውነት አልገባኝም፣ እንዴት ያለ ዓውድ ነው በብርሃን ፍጥነት ሀብት የሚያስገኘው?
  • አልገባኝም ካሉማ እነግርዎታለሁ።
  • ይንገሩኝ፡፡
  • ሲነጋ ሀብት የሚፈጠርበት ሥልት አንድና አንድ ነው።
  • ምንድነው?
  • ከከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር ግንኙነት የመፍጠር ሥልት ነው፣ ወንድም ወይም ዘመድ አዝማድ የመሆን ሥልት፡፡
  • እሱን ነው እንዴ? ይህንንማ እኛም ገምግመናል።
  • ምን ብላችሁ ገመገማችሁት?
  • በዝተዋል ብለን ገምግመናል።
  • እነ ማን ናቸው የበዙት?
  • አካም አካም የሚሉ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን የፓርቲያቸውን የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ አጠናቀው ወደ ቢሯቸው ሲመለሱ ቢሯቸው ውስጥ አማካሪያቸው አንድ ነገር በመተመስጦ እያነበበ አገኙት]

  • ምንድነው እንደዚህ መስጦ የያዘህ ጉዳይ?
  • መጡ እንዴ ክቡር ሚኒስትር? የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያወጣውን መግለጫ እያነበብኩ ነው።
  • ግን እኮ ፊትህ ላይ የመገረም ስሜት ይነበባል።
  • አዎ፣ መግለጫው ላይ የተመለከትኳቸው አንዳንድ ነጥቦች ትንሽ አስገርመውኝ ነው።
  • እንዴት? የትኛው ነጥብ ነው ያስገረመህ?
  • ለምሳሌ እዚህ ጋ፣ የፓርቲው አባላት የጋራ አመለካከት እንዲይዙ በማድረግ ውጤት መመዝገቡን አረጋግጧል ይላል።
  • አዎ፣ ምኑ ነው የገረመህ?
  • አሁን ግጭት በሚካሄድበት ክልል የፓርቲ አመራሩ የጎራ መደበላለቅ ለግጭቱ ምክንያት ነው ሲባል ነበር ብዬ ነው፡፡
  • እሱ እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው።
  • እንደዚያ ከሆነ ጥሩ፣ ግን ደግሞ ዝቅ ብሎ በፓርቲው የአመራር ዲሲፕሊን መሻሻሉና የመፈጸምና ማስፈጸም አቅም መጎልበቱ ተረጋግጧል ይላል።
  • አዎ፣ ልክ ነው።
  • በቅርቡ ግን አንድ ከንቲባና ሌሎች ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮች በማዳበሪያ ዝርፊያ ተጠርጥረው ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ተነግሮ ነበር።
  • እሱ እንዳለ ሆኖ፡፡
  • እንዳለ ሆኖ ሲሉ ምን ለማለት ነው?
  • ችግሩ አለ ለማለት ነው ወይም…
  • እ?
  • ወይም ደግሞ ተገምግሟል ማለቴ ነው።
  • ግን አይጋጭም?
  • አይጋጭም፣ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ህፀፆች እንዳይደገሙ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
  • የምን አቅጣጫ?
  • እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት በቀጣይ የአመራር አቅም ግንባታ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል፡፡
  • ወደ መጨረሻ አካባቢ ደግሞ በግብርና መስክ ምርትና ምርታማነትን ለማደሳደግ በተሠራው ሥራ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል ይላል፡፡
  • አዎ፣ ልክ ነው፡፡
  • ግን በበርካታ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት አርሶ አደሩ የግብርና ሥራውን ለማከናወን እንዳልቻለ ይታወቃል፡፡
  • እሱ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡
  • የአፈር ማዳበሪያም በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ማድረስ እንዳልተቻለና ይህም ከቅሬታ አልፎ አርሶ አደሩን አስቆጥቷል፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም የተቃውሞ ሠልፍ ወጥተዋል፡፡
  • እሱ እንዳለ ሆኖ፡፡
  • እንደዚያ ነው?
  • አዎ፣ ችግሩ ተገምግሟል ቢሆንም የተገኘውን ስኬት የሚያደበዘዝ ሆኖ አላገኘነውም፡፡
  • እዚህ ጋ ደግሞ እንዲህ ይላል፡፡
  • ምን ይላል?
  • በኢትዮጵያ ታምርት መርሐ ግብር የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የነበሩባቸው ችግሮች ተፈትተው የማምረት አቅማቸው እንዲያድግ ተደርጓል ይላል፡፡
  • ልክ ነው።
  • በዚህም ምክንያት በርካታ ባለሀብቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ማድረግ እንደተቻለና ምርትና ምርታማነት እንዳደገ ይገልጻል።
  • ልክ ነው፡፡
  • ግን እኮ አብዛኞቹ ኢንደስትሪዎች የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንዳልቻሉ እየገለጹ ነው፡፡
  • እሱ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡
  • በተደረገው ጥረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት ረገድ ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል ይላል።
  • አዎ፣ በዚህ ረገድ ትልቅ ስኬት ነው የተመዘገበው፡፡
  • እንዴት?
  • ምን እንዴት አለው?
  • አሁንም የምግብ ዘይት ከጂቡቲ እያስገባን አይደለም እንዴ? ስኳርስ ቢሆን ከውጭ አይደለም የሚገባው?
  • እሱ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡
  • ታዲያ በአገር ውስጥ ተተኩ የተባሉት ምን ዓይነት ምርቶች ናቸው?
  • ለምሳሌ አንድ ሁለት መጥቀስ እችላለሁ፡፡
  • ችግር የለም አንድም ቢሆን ይበቃል፡፡
  • ለምሳሌ ዩኒፎርም መጥቀስ ይቻላል፡፡
  • የምን ዩኒፎርም?
  • የፀጥታ አስከባሪዎች!
People are also reading