Home Back

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

ethiopianreporter.com 2024/7/6
  • የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ?
  • እንኳን ምላሻቸውን ቅሬታውንም አልሰማሁም።
  • እንዴት?
  • አልሰማሁማ? የምን ቅሬታ ቀርቦባቸው ነው?
  • ሰሞኑን ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ውድና ቅንጡ አውሮፕላን ተከራይተዋል የሚል ቅሬታ ነው የቀረበባቸው።
  • እንዴት እንዲህ ዓይነት ቅሬታ ይቀርብባቸዋል?
  • ለምን አይቀርብም?
  • የአገር መሪ አይደሉም እንዴ?
  • የሆኑስ እንደው?
  • ሥልጣናቸውን ሚመጥን አውሮፕላን መከራየት ይኖርባቸዋላ?
  • እሳቸው ግን እንደዚያ አላሉም፡፡
  • እና ምን አሉ?
  • ውድ ወገኖቼ፣ የኬንያን ሕዝብ ሀብት የመጠበቅና በአቅማችን እንድንኖር የማድረግ ኃላፊነት አለብኝ። ይህንንም እንደ መሪ ለመተግበር ቁርጠኛ ነኝ ነው ያሉት፡፡
  • ምላሽ ሰጡ ያልሽው ይሄንን ነው?
  • ይሄ ብቻ አይደለም።
  • ሌላ ምን አሉ?
  • ወደ አሜሪካ የተጓዝኩት ውድና ቅንጡ አውሮፕላን ተከራይቼ መስሏችሁ የተሰማችሁን ቅሬታ አስተውያለሁ። ነገር ግን አሉ…
  • እሺ…. ነገር ግን ብለው ምን አሉ?
  • ለዚህ ጉዞ ያወጡት አጠቃላይ ወጪ…
  • እ… የኬንያን ገጽታ ለመገንባት የዋለ ነው አሉ?
  • ኧረ የምን ገጽታ ግንባታ… ምን በወጣቸው?
  • እንዴት? እና ምንድነው ያሉት?
  • ለጉዞው ያወጡት አጠቃላይ ወጪ በኬንያ አየር መንገድ ቢጓዙ ከሚያወጡት ወጪ ያነሰ መሆኑን ነው የተናገሩት።
  • ምንድነው ታዲያ አንቺን እንዲህ ያስደነቀሽ?
  • ሁለት ነገሮች።
  • እሺ አንደኛው ምንድነው?
  • አንደኛው ለሕዝብ ቅሬታ ዋጋ ሰጥተው ምላሽ መስጠታቸው ነው።
  • እሺ ሁለተኛውስ?
  • ሁለተኛውማ ይህ ጥያቄ የተነሳው እዚህ አገር ቢሆን የሚለው ነው ያስደነቀኝ።
  • እዚህ ቢሆን ምኑ ያስደንቃል?
  • ምን ብላችሁ ምላሽ እንደምትሰጡ አስቤ ነዋ?
  • ምን ምላሽ ልንሰጥ እንችላን?
  • በእርግጠኝነት ሁለት ምላሾችን ትሰጣላችሁ።
  • ምን ብለን?
  • በመጀመርያ የምትሉት ምን መሰለህ?
  • እ…?
  • ያልሰጣችሁኝን በጀት አትጠይቁኝ፡፡
  • ወይ አንቺ… እሺ ሁለተኛውስ?
  • ሁለተኛው?
  • እ…?
  • ወጪውን የሸፈኑት የሌላ አገር ፕሬዚዳንቶች ናቸው። ከፈለጋችሁ…
  • ከፈለጋችሁ ምን?
  • ከፈለጋችሁ ሂዱና ጠይቁ ትላላችሁ።
  • ማንን?
  • ፕሬዚዳንቶቹን!

[ክቡር ሚኒስትሩ አሁን አምባሳደርነት የሚያገለግሉትን የቀድሞ ሚኒስትር ወዳጃቸውን ይዘው የጎርጎራ ፕሮጀክትን አስጎብኝተው እየተመለሱ ነው]

  • ጉብኝቱ እንዴት ነበር አምባሳደር?
  • አምባሳደር ብለህ ባትጠራኝ ደስ ይለኛል?
  • ለምን?
  • በስሜ እንድትጠራኝ ነው የምፈልገው።
  • እንደዛማ ትክክል አይሆንም?
  • ምን ችግር አለው?
  • አገርዎትን በአምባሳደርነት ሲያገለግሉ ቆይተው?
  • ቢሆንም በስሜ እንድትጠራኝ ነው የምፈልገው ካልሆነ ግን…
  • እ… ካልሆነ ምን?
  • ካልሆነ እኔም አንተን ክቡር ሚኒስትር ብዬ አልጠራህም፡፡
  • ታዲያ ምን ብለው ሊጠሩኝ ነው?
  • የወደፊት አምባሳደር፡፡
  • ኪኪኪኪ… ተጫዋች እኮ ነህ። ግን እንዴት ነበር?
  • ምኑ?
  • ለአምባሳደሮች የተዘጋጀው ጉብኝት?
  • እኔ ለምን እንዳስጎበኙንም አልገባኝም።
  • እንዴት?
  • ብዙዎቻችን ሚኒስትር እያለን የምናውቃቸውን ፕሮጀክቶች ነው የጎበኘነው።
  • ቢሆንም ፕሮጀክቶቹ አሁን የደረሱበትን ደረጃ መመልከቱ ችግር ያለው አልመሰለኝም። አለው እንዴ?
  • አብዛኞቻችን ፕሮጀክቶቹን እናውቃቸዋለን። በዚያ ላይ ደግሞ እኔ ብዙም አይገባኝም።
  • ምኑ?
  • የፕሮጀክቶቹ ፋይዳ፡፡
  • እንዴት እንደዛ ይላሉ አምባሳደር?
  • ወደፊት ፋይዳ ይኖራቸው ይሆናል ነገር ግን አሁን ላይ ካለው የአገሪቱ ሕዝብ ፍላጎት አንፃር የረባ ፋይዳ ይኖራቸዋል ብዬ አላምንም።
  • እንዴት?
  • በአጭሩ ልግለጽልህ?
  • እሺ…
  • የፓርኮቹ ግንባታና በአንድ ወቅት በመላ አገሪቱ የተገነቡ የእግር ኳስ ስታዲየሞችን ያስታውሰኛል።
  • እንዴት?
  • በቃ ለእኔ ይመሳሰሉብኛል።
  • ሁለቱን ደግሞ ምን ያመሳስላቸዋል?
  • ሁለቱም ከሚፈለጉበት ጊዜ ቀድመው መገንባታቸው።
  • አልገባኝም?
  • የእግር ኳስ ስታዲየሞች በሁሉም ክልሎች ቢገነቡም አገልግሎታቸው ግን ሌላ ሆኗል።
  • ምን ሆኗል?
  • የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ማክበሪያ፡፡
  • ፓርኮቹ ግን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ማክበሪያ አይሆኑም።
  • ብሔር ብሔረሰቦችማ ቀናቸውን ማክበሪያ ቦታ አግኝተዋል።
  • ፓርኮቹ ግን የቱሪስቶች መዳረሻ ይሆናሉ።
  • መቼ?
  • አገሪቱ ስትረጋጋ።
  • ለዛ እኮ ነው ፕሮጀክቶቹ ለዚህ ትውልድ አይጠቅሙም የምልህ።
  • እና ለዚህ ትውልድ የሚጠቅሙት ፕሮጀክቶች ምንድናቸው?
  • ፓርኮቹን አቆይቶ ፕሮጀክቶቹን መጨረስ።
  • የትኞቹን?
  • የመስኖ ፕሮጀክቶቹን!
People are also reading