Home Back

ኢሠማኮ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የደመወዝ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ ያቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ተቃወመ

ethiopianreporter.com 2024/10/5
የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሜሪትና የደመወዝ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን ተናገረ፡፡

ኢሠማኮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቦርድ ሰብሳቢ መሆን የለባቸውም የሚል ሐሳብ ያቀረበበት ምክንያት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦርዱን በሰብሳቢነት ሲመሩ የሚያሳልፉት ውሳኔ፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲተላለፍ፣ የምክር ቤቱም ሰብሳቢ እሳቸው በመሆናቸውና የራሳቸውን ውሳኔ ተመልሰው ስለሚያገኙትና ድርብ ኃላፊነት ስለሚሰጥ እንደሆነ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሻሻያ እንዲደረግ በጽሑፍ ባቀረበው ሐሳብ ላይ ገልጿል፡፡  

የደመወዝ ቦርድ አወቃቀር ሥርዓትና ስብጥር ላይም የሠራተኛ ተወካዮች ስለሚካተቱበት ሁኔታ መመልከት እንደነበረበትም ጠቅሷል፡፡ የደመወዝ ቦርዱን ከሚመለከተው አንቀጽ ሌላ በረቂቁ ውስጥ ማሻሻያ ያስፈልገዋል ብሎ የጠቀሰው ‹‹አንድ ሠራተኛ ከሁለት ጊዜያት በላይ የብቃት ማነስ ከታየበት ከሥራ ይሰናበታል›› በሚል የተደነገገውን የሚመለከት ነው፡፡ በኢሠማኮ እምነት ይህንን ድንጋጌ መተግበር አስቸጋሪ ነው፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የሠራተኛ አስተዳደርና ጠንካራ የምዘና ሥርዓት ባልተዘረጋበትና እንዲሁም ይህንንም ምዘና ሥርዓት የሚያሳልጥ ጠንካራ ተቋም በሌለበት ሁኔታ፣ በቀጥታ የሥራ ውል ከሚቋረጥ ሌሎች አማራጮችን ማየት ይገባል፤›› በማለት ይህ ድንጋጌ ሊሻሻል እንደሚገባ ኢሠማኮ አስታውቋል፡፡

ኢሠማኮ ይህንን ድንጋጌ ከመተግበር ይልቅ አማራጭ ያለውንም ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ከሁለት ጊዜያት በላይ የብቃት ማነስ ታይቶበታል የተባለውን ሠራተኛ፣ በተመደበበት የሥራ መደብ ላይ የተለያዩ ሥልጠናዎችን መስጠትና ችሎታውን እንዲያሳድግ ማድረግ እንደ አማራጭ ሊታይ እንደሚገባ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ስለዚህ በዚህ አንቀጽ ውስጥ የሙያ ላይ ሥልጠናዎችን በመስጠት ክህሎቱን እንዲያዳብር አድርጎ ማቆየት የሚያስችል አንቀጽ ይኖርበታል ብሏል፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሥራዎችንና የአገልግሎቶች አሰጣጥን በሦስተኛ ወገን (Outsourcing) የማሠራት አግባብነትን በተመለከተው የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ ዙሪያም ያለውን አቋም አንፀባርቋል፡፡ ይህ አንቀጽ ማሻሻያ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከረቂቅ አዋጁ መውጣት አለበት ብሏል፡፡

ሥራዎችን በሦስተኛ ወገን የማሠራት ተግባር በሌሎች አገሮችም የተለመደና የሚታወቅ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ እንዲህ ያለው አሠራር ውጤታማ ባለመሆኑ፣ በረቂቁ በተቀመጠው መንገድ ድንጋጌውን መተግበር አስቸጋሪ እንደሚሆን ያለውን ሥጋት ገልጿል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የጠቀሰው የአገር ውስጥ ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችን ነው፡፡

‹‹ይህንን ሕጋዊ ተግባር አንዳንድ ወገኖች ለዜጎች ጉልበት ብዝበዛ እየተጠቀሙበት በመሆኑ በርካታ ጫጫታ ፈጥሯል፤›› ያለው የኢሠማኮ ማብራሪያ፣ በዚህ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴውም ሆነ ከሥራና ከክህሎት ሚኒስቴር ጋር በነበረው ውይይት ላይ ተነስቶ እንደነበር አስታውሷል፡፡

በመሆኑም ምንም ዓይነት የአሠራር ሥርዓት ባልተዘረጋበት ሁኔታ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ መካተቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶቹ ሥራዎቹንና አገልግሎት አሰጣጡን በሦስተኛ ወገን ማሠራት የሚለው አንቀጽ ከአዋጁ ውስጥ ቢወጣ የተሻለ ነው ብሏል፡፡

የዚህ አንቀጽ ከረቂቅ አዋጁ መውጣት አለበት የሚለውን ሐሳብ ያጠናክርልኛል ብሎ ያስቀመጠው፣ ሥራዎችን በሦስተኛ ወገን ማሠራት የሠራተኛዎችን የሥራ ዋስትና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ በሦስተኛ ወገን የሚከናወኑ ሥራዎች  ለብልሹ አሠራር የሚያጋልጡ በመሆናቸው የዚህ አንቀጽ ጉዳይ በድጋሚ በደንብ ሊታይ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

በረቂቅ አዋጁ የመንግሥት ሠራተኞች የአስተዳደርና ፍርድ ቤቶችን በተመለከተ ‹‹ሕገ መንግሥቱ በቀጥታ እንዲደራጁ ከፈቀደላቸው አምስት ተቋማት ውስጥ መደበኛ ፍርድ ቤቶችና የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች የሚጠቀሱ ናቸው፤›› በማለት፣ ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲደራጁ በሕገ መንግሥት የተሰጠ ነፃነት ሆኖ ሳለ፣ በረቂቅ አዋጁ አስተዳደር ፍርድ ቤቱ ተጠሪነቱ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መሆኑ የገለልተኝነት ጥያቄ ከማስነሳቱም በላይ ተደራሽ ሊሆን ስለማይችል ይህ አንቀጽ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ገልጿል፡፡

በረቂቁ በተቀመጠው መሠረት ይሠራ ከተባለ የጣልቃ ገብነትን ጉዳይ የሚቀር አለመሆኑን፣ ስለሆነም የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ተጠሪነት ቢያንስ ለሌላ አካል መሆን እንደሚኖርበት አሳስቧል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዞም ዳኞችን የሚመድበው፣ ደመወዝ የሚከፍለውና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን የሚሰጠው ኮሚሽኑ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን ተፅዕኖም ጠቅሷል፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ዳኞች ነፃ ሆነው ሥራቸውን በሕግና በሕግ ብቻ ይሠራሉ ለማለት የሚያስችል ሁኔታ ስለሌለ ይህ አንቀጽ ድጋሚ በትክክል ሊታይ ይገባል ብሏል፡፡

በመንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የተሰጠበት ሌላው ጉዳይ፣ ‹‹የመንግሥት ሠራተኞች የመደራጀት መብት››ን የተመለከተ ነው፡፡

ኢሠማኮ የመንግሥት ሠራተኞች በሠራተኛ ማኅበር የመደራጀት ጉዳይን አስመልክቶ በረቂቁ አዋጅ ከተዘጋጀው የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች የተወሰዱ የማሻሻያ ሐሳቦች የሠፈረውን ድንጋጌ ተንተርሶ በሰጠው አስተያየት፣ በተለይ የመንግሥት ሠራተኛ የመደራጀት መብት ላይ እየታየ ያለውን ችግር በስፋት አብራርቶታል፡፡

በመንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ውስጥ፣ ‹‹የሠራተኞች በሠራተኛ ማኅበር የመደራጀት ጉዳይ በኮሚሽኑ አነሳሽነት የሚሠራ አይደለም›› በማለት የተደነገገውን ድንጋጌ፣ ‹‹ኮሚሽኑ ፈቃጅም ከልካይም ሊሆን አይገባም›› ሲል ኢሠማኮ ገልጾታል፡፡ በሠራተኛ ማኅበር የመደራጀት መብት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 4፣ አንቀጽ 31 እና 42 ድንገጌ መሠረት የተደገፈ ከመሆኑም በላይ፣ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የፈረመችበት በመሆኑ፣ መደራጀት መብት እንጂ ፈቃድና ከልካይ ሊኖረው የማይገባ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ አንቀጹ የተገለጸበትን መንገድ ተችቷል፡፡

በረቂቁ አንቀጽ የተቀመጠበት መንገድም ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መካከል እ.ኤ.አ. በ1948 የወጡት የዓለም የሥራ ድርጅት ኮንቬንሽን ቁጥር 87 እና 98፣ በሠራተኛ ማኅበር ስለመደራጀት መርሆና የኅብረት ስምምነት ስለመደራደር ከወጣው ድንጋጌ ጋር ይጋጫል ብሏል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቃል ኪዳን አንቀጽ 20 ድንጋጌ ማንም ሰው በሰላም የመሰብሰብና ማኅበር የመቋቋም ነፃ መብት እንዳለው፣ እንዲሁም በአንቀጽ 23 ደግሞ ማንም ሰው የራሱን ጥቅም ለማስከበር የሠራተኛ ማኅበር የማቋቋምና አባል የመሆን መብት እንዳለው በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ፣ እንዲህ ያለው አንቀጽ በአዋጁ መካተት እንደሌለበት ኢሠማኮ አቋሙን ገልጿል፡፡

በዚህም የመንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ የሠራተኞች በማኅበር መደራጀት መርሆ በመብት አጠባበቅ ረገድ ሐሳብን ሊገልጽ የሚችልበት መንገድ ለመዘርጋት ብቻም ሳይሆን፣ የሥራ ሁኔታዎችን ለማሻሻል ሰላምን ለመመሥረት መሆኑ ከግምት ሊገባ ይገባል ብሏል፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ሠራተኞችን የመደራጀት መብት ያልጠበቀ አዋጅ ሙሉ ሊሆን እንደማይችል አመልክቷል፡፡ ሕገ መንግሥታዊና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን ወደ ጎን በማለት የመንግሥት ሠራተኛው በሠራተኛ ማኅበር እንዳይደራጅ በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 3 በግልጽ መከልከሉ አግባብነት የሌለው መሆኑን አስታውሷል፡፡ ይህ ክልከላ በዓለም የሥራ ድርጅት በተደጋጋሚ ጊዜ ቅሬታ ያቀረበበት መሆኑን የገለጸው ኢሠማኮ፣ በዚህም አዋጅ ሠራተኞች በማኅበር መደራጀት መብታቸው መሆኑን በግልጽ በማመላከት የአደረጃጀቱን ዝርዝር ሁኔታን አካትቶ መውጣት እንደሚጠበቅበት አሳስቧል፡፡

‹‹መንግሥትም የተደራጀ ሠራተኛን ለመምራትና በፖሊሲው ላይ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት መደራጀት ወሳኝ በመሆኑ፣ የሠራተኛው በማኅበር የመደራጀት የሰብዓዊ መብት በመሆኑ ሊታይ ይገባል ብቻ ሳይሆን፣ የሠራተኞች መደራጀት መብት መንግሥት ሊደግፍና ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር ይገባል፤›› በማለት በዚህ ላይ ያለውን አቋም አንፀባርቋል፡፡

የመደራጀት መብት በአሁኑ ወቅት ትልቅ ፈተና እየሆነ መምጣቱን የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ገልጸዋል፡፡ በተለይ የውጭ ኩባንያዎች ሠራተኞች እንዳይደራጁ ክልከላ በማድረግ ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡ ከውጭ ኩባንያዎችም የቻይና ኩባንያዎች ሠራተኞች እንዳይደራጁ ክልከላዎችን በማድረግ የሠራተኞችን መብት እየነኩ መሆናቸውን፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የቻይና ኩባንያዎች 90 በመቶ ያህሉ የሠራተኞች በማኅበር ያልተደራጀባቸው መሆናቸውን፣ ለማደራጀት የተደረጉ ሙከራዎች ሙሉ በሙሉ አለመሳካታቸውን ከኢሠማኮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡   

People are also reading