Home Back

የሻምፒዮንስ ሊጉ የፍጻሜ ጨዋታ ነገ ምሽት በዌምብሌይ ስታዲየም ይደረጋል

fanabc.com 2024/10/5

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2023/24 አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ነገ ምሽት በእንግሊዙ ዌምብሌይ ስታዲየም ይደረጋል፡፡

ምሽት 4 ሰዓት ላይ ሊደረግ ቀጠሮ በተያዘለት ታላቁ የፍጻሜ ጨዋታ የአውሮፓ ሻምፒዮንሰ ሊግ ንጉሶቹ ሪያል ማድሪድ እና የጀርመኑ ክለብ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ የባለ ትልቁ ጆሮ ዋንጫ ለማንሳት ይፋለማሉ፡፡

በጨዋታው ሎስ ብላንኮቹ የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ለ15ኛ ጊዜ ለማንሳት ወደ ዌምብሌይ የሚያቀኑ ሲሆን÷ በሌላ በኩል ሳይጠበቁ ለፍጻሜ የደረሱት ቦሩሲያ ዶርትመንዶች ዋንጫውን ለሁለተኛ ጊዜ ለማንሳት ብርቱ ፍልሚያ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

የቡድን ዜናዎችን በተመለከተ በሪያል ማድሪድ በኩል ኦስትሪያዊው ተከላካይ ዴቪድ አላባ እና ፈረንሳዊው አማካይ ኦውሪሊየን ሹዋሜኒ በጉዳት ምክንያት ከነገ ምሽቱ ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ÷በአንጻሩ ስፔናዊው ተከላካይ ናቾ ፈርናንዴዝ ከጉዳት አገግሞ ቡድኑን በአምበልነት እንደሚመራ ይጠበቃል፡፡

በዌምብሌዩ የፍጻሜ ጨዋታ ጀርመናዊው አንጋፋ የመሃል ክፍል ተጫዋች ቶኒ ክሩስ ለክለቡ የመጨረሻ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ሪያል ማድሪድ ለፍፃሜው የደረሠው የጀርመኑን አር ቢ ሌብዚሽ፣ የእንግሊዙን ማንቸስተር ሲቲን እንዲሁም የጀርመኑን ባየርን ሙኒክን በጥሎ ማለፉ ሒደት በማሸነፍ ለፍጻሜ የደረሰ ሰሆን÷ ከማድሪድ ድሎች በስተጀርባ ተሰናባቹ አማካይ ቶኒ ክሩስ ስሙ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

ዶርትሙንዶች ከ11 ዓመት በፊት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለፍጻሜ ደርሰው በባየርን ሙኒክ ተሸንፈው ዋንጫውን ያጡበትን የዌምብሌይ ስታዲየም አሳዛኝ ምሽት በደስታ ለመቀየር ወደ ለንደን ከተማ ያቀናሉ፡፡

በዶርትሙንድ በኩል ራሚ ቤንስቤኒ፣ ጁሊየን ዱራንቬሌ እና ማቲው ሞሬይ በጉዳት እና በህምም ምክንያት ከቅዳሜው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ÷ ኮትዲቯራዊው አጥቂ ሰባስቲያን ሃለር ከቡድኑ ጋር ልምምድ አለማድረጉ ተጠቁሟል፡፡

ቢጫ ለባሾቹ በምድብ ማጣሪያው ኤሲ ሚላን፣ ኒውካስትል ዩናይትድ እና ፓሪስ ሳን ዠርሜን በመብለጥ የምድቡ መሪ ሆነው ወደጥሎ ማለፍ ዙር መግባታቸው ይታወሳል። በጥሎ ማለፉ ደግሞ የሆላንዱን ፒኤስ ቪ አይንድሆቨን፣ የስፔኑን አትሌቲኮ ማድሪድን እንዲሁም የፈረንሳዩን ፒ ኤስ ጂን ከውድድሩ በማስወጣት ለፍጻሜ ደርሰዋል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ባደረጓቸው ያለፉት 5 ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ ሁለት ጊዜ ፤ ዶርትመንድ ደግመ አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት አጠናቅቀዋል፡፡

ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ እስካሁን አስራ አራት ጊዜ እርስ በርስ የተገናኙ ሲሆን ሪያል ማድሪድ ስድስት ጊዜ ሲያሸንፍ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በአንፃሩ ሶስት ጨዋታዎችን አሽንፏል። ቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

People are also reading