Home Back

በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ለሚሠሩ ሠራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ሊወስን ነው

ethiopianreporter.com 2024/7/6
spot_img

በኢትዮጵያ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ለሚሠሩ ሠራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ መጠንና የማትጊያ ሥርዓቶች በወጥነት እንዲተገበር በአዋጅ መወሰኑ ታወቀ፡፡

በአሁኑ ወቅት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲኖር የሚያስችል ሕግ ባይኖርም በልዩ በኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ግን ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ባለፈው ሳምንት በፀደቀው የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ አመላክቷል፡፡

በኢኮኖሚ ዞኖች የሚመለከተው ይህ አዋጅ ካካተታቸው አንቀጾች መካከል የሠራተኞችን ደመወዝና ተያያዥ መብቶችን የሚመለከተው ይገኝበታል።

በዚህም መሠረት የኢኮኖሚ ዞኖችን እንዲያስተዳድር ሥልጣን የተሰጠው ኮሚሽን ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከሠራተኛ ጉዳይ ቢሮዎች፣ ከሠራተኞች ተወካዮችና ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር የሠራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝና ማትጊያ ሥርዓት የሚዘረጋ መሆኑ ተደንግጓል፡፡

ይህንኑ ጉዳይ የተመለከተው የአዋጁ አንቀጽ ኮሚሽኑ ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን፣ የደመወዝ ዓይነት፣ የማትጊያ ሥርዓቶች በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ መተግበር የሚኖርበት መሆኑንም ጠቅሷል፡፡ 

ከዚህም ሌላ የሠራተኞች የመድኅንና ሌሎች ለሠራተኞች የሚጠበቁ መብቶችን ለመወሰን፣ ተግባራዊ ለማድረግና ወጥ የሆነ ሥርዓት ለመዘርጋት ኮሚሽኑ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሠራተኛና ጉዳይ ቢሮዎች፣ ከሠራተኛ ተወካዮችና ከባለሀብቶች ጋር በትብብር የሚሠራ መሆኑንም በአዋጅ ከመጠቀሱም በላይ ኮሚሽኑ እነዚህን ጉዳዮች ወጥ በሆነ መንገድ የሠራተኞችና ድርጅቶች መካከል በሚፈረሙ የሥራ ውሎች ውስጥ መካተታቸውን ማረጋገጥ እንደሚኖርበትም ደንግጓል፡፡ 

ለዚህ ሥራ የሚቋቋምው ኮሚቴም የሠራተኞች መብቶችና ግዴታዎች በኢንቨስትመንት ተቋሙ ማኔጅመንትና በሠራተኞች መታወቃቸውንና በአግባቡ መተግበራቸውን የማረጋገጥና ተከታታይና ወጥ የሆኑ የምክክርና ግንኙነት መድረኮችን መፍጠር ይኖርበታል፡፡ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ውጥረትና አለመግባባቶችን የመከላከል ኃላፊነት ጭምር ለዚሁ ኮሚቴ የተሰጠ ኃላፊነት ሆኗል፡፡ 

ለምክክርና አማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች ቅድሚያ በመስጠት የግልና የወል የሥራ ጉዳዮችና አለመግባባቶችን በሆነ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል፣ በአሠሪና ሠራተኛ ሕግና በዚህ አዋጅ የተመለከቱ መርሆዎችን መሠረት ያደረገ ሥርዓት የሚዘረጋ ሲሆን፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ክህሎትና ቴክኖሎጂ የዕውቀት፣ ስለመደረጉና ምርታማነት ስለመጨመሩ የማረጋገጥ ኃላፊነትም ይኖርበታል፡፡ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን ተግባራትን የማከናወን ሌሎች ተግባራትን ኮሚሽኑ በሚሰጠው ማረጋገጫ መሠረት ለልዩ ኢኮኖሚ ዞን አልሚ ወይም አስተዳዳሪ ወይም ሠራተኛ፣ ሥራ አስኪያጅ፣ ከዋና መሥሪያ ቤት ለሚመጣ ሥራ አስፈጻሚ ለቦርድ አባል፣ ወይም ለከፍተኛ ባለሙያ ለሦስት ዓመታት የሚያገለግል መመላለሻ ቪዛ ወይም የመኖሪያ ፈቃድ ሊሰጥ የሚችል መሆኑንም በዚሁ አዋጅ ተወስቷል፡፡ 

በአዋጁ የሠራተኞችን ጉዳይ የሚመለከቱ ሌሎች ድንጋጌዎችንም ያካተተ ሲሆን፣ በተለይ የውጭ አገር ዜጎች የሥራ ፈቃድ፣ የመኖሪያ ፈቃድ፣ ቪዛና የክህሎት ሽግግርን በተመለከተ የሥራ ሁኔታ ቁጥጥርና አስተዳደር የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ተፈጻሚ የሚያደርግ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ ይህም ድንጋጌ ቢኖርም በሕግ፣ በኅብረት ስምምነት ወይም በሥራ ደንብ ለሠራተኛ የተሰጡ ጥቅሞችን ሳይነካ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ በሚገኘ አሠሪዎችና ሠራተኞች መካከል የልዩ ኢኮኖሚ ዞንን ልዩ ባህሪ ግምት ውስጥ ያስገባ የሥራ ውል ድርድር እንዲደረግ ኮሚሽኑ ሊፈቅድ የሚችል መሆኑንም በአዋጁ ተጠቅሷል፡፡ 

ለሕግ ተቃራኒ እስካልሆነ ድረስ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በየቀጣሪ ድርጅቶቹ የንግድ ሥራ አካሄድና በሠራተኞች መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ይተዳደራሉ፡፡ ኮሚሽኑ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ ሠራተኞችን የመመልመል፣ ሥልጠና የመስጠት፣ የመመዝገብ፣ የመመደብና የመቅጠር ሒደት ለማሳለጥ እንዲቻል ከአካባቢው የሠራተኞች ጉዳይ ቢሮና ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር በእያንዳንዱ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሥራ አገልግሎት ተቋም እንዲደራጅ ኃላፊነትም ተሰጥቶታል፡፡  ማንኛውም የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አስተዳዳሪ ወይም ድርጅት ሠራተኞችና ሌሎች ነዋሪዎች ደኅንነታቸውና ጤንነታቸው በተጠበቀ ከባቢ የሚሠሩ መሆኑን ለማረጋገጥ አስገዳጅ የሥራ ጥበቃ ዕርምጃዎችን የመውሰድ ግዴታ እንዳለበትም ያመለክታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ አዋጅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የአገር ውስጥና የውጭ ባንኮች አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና የራሱን የቻለ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሪፎርም በማድረስ የአሠራር ሥርዓት እንደሚዘረጋ አመላክቷል፡፡ 

በወጣው አዋጅ ውስጥ በግልጽ እንደተቀመጠው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ወይም ይሁንታ ያገኙ የውጭና የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት በልዩ ኢኮኖሚ ዞን አገልግሎት የማቅረብ መብት አላቸው፡፡

በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ በፋይናንስ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ ተቋማት የሚመረጡበት መሥፈርት፣ ደረጃና አሠራር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን መሆኑንም አዋጁ አመልክቷል፡፡

የፋይናንስ ተቋማት ወደ ዞኑ ገብተው መሥራት የሚችሉት ለዚሁ አገልግሎት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ሲያገኙ ሲሆን የፈቃድ አሰጣጡም ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን ይሆናል ይላል፡፡

በኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የፋይናንስ አገልግሎትን በተመለከተ በዚህ አዋጅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጠው ሥልጣን ራሱን የቻለ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት የሚዘረጋ ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡ 

ይህንንም ‹‹አግባብነት ባለው ሕግ መሠረት የተሰጡ የባለሀብቶች መብቶች እንደተጠበቁ ሆኖ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የልዩ ኢኮኖሚ ዞንን ሳቢነት፣ ተወዳዳሪነትንና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ራሱን የቻለ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሪፎርም ያደርጋል፣ የአሠራር ሥርዓት ይዘረጋል፤›› በሚል ገልጾታል፡፡ 

People are also reading