“አንድ ቢሊዮን ዶላር እስክናገኝ ጥሪያችንን እንቀጥላለን” - ዩኤንኦቻ
በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ፣ በኢትዮጵያ የነፍስ አድን ርዳታ ለማቅረብ አንድ ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ያስታወቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለዚሁ ዓላማ ትላንት ማክሰኞ፣ በስዊዘርላንድ - ጄኔቫ በተካሔደ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት፣ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተስፋ ቃል መገባቱን ገለጸ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ወይም በምኅጻሩ ዩኤን-ኦቻ ምክትል ቃለ አቀባይ ጀንስ ላርክ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ከጄኔቫ በሰጡት የስልክ ቃለ መጠይቅ፣ ገቢው የተገኘው ከ20 ለጋሾች መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ አስቸኳይ ርዳታ የሚያስፈልገው አንድ ቢሊዮን ዶላር እስኪገኝ ድረስም ጥሪ ማቅረባችንን እንቀጥላለን፤ ብለዋል፡፡