Home Back

የቱርኩ የመሐል ተከላካይ ዴሚራል የሁለት ጨዋታ እገዳ ተጣለበት

fanabc.com 2024/10/5

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱርኩ የመሐል ተከላካይ ሜሪህ ዴሚራል ሀገሩ ቱርክ ከኦስትሪያ ጋር በነበረው ጨዋታ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ባሳየው አወዛጋቢ የደስታ አገላለፅ ምልክት በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ሁለት ጨዋታ እንዲታገድ ተደርጓል፡፡

የ26 ዓመቱ ዴሚራል በአውሮፓ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ኦስትሪያ ላይ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን ለመግለፅ የተጠቀመበትን ምልክት የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ሲመረምር ቆይቷል፡፡

በማህበሩ ምርመራ መሰረትም ሜሪህ ዴሚራል የተጠቀመው የአጅ ጣት ምልክት ግራጫ ተኩላዎች ወይም ግሬይ ዎልቭስ በመባል የሚጠራውን የቱርክ ብሄራዊ ንቅናቄ ፓርቲን የሚወክል ምልክት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

በዚህም መሰረት ተከላካዩ በእግር ኳስ ስፖርት ነክ ያልሆነ መልዕክት በማስተላለፉ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የሁለት ጨዋታ እግድ ተጥሎበታል።

በዚህም ነገ ምሽት ቱርክ ከኔዘርላንድስ ጋር በምታደርገው ጨዋታ አይሰለፍም፡፡

የተጫዋቹን የደስታ አገላለፅ ምልክት ተከትሎ ቱርክ የጀርመን አምባሳደርን መጥራቷ የተገለፀ ሲሆን፤ የጀርመኑ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፋዘር “የቱርክ ቀኝ ጽንፈኞች በእኛ ስታዲየም ውስጥ ቦታ የላቸውም” ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡

የተጨዋቹ ፖለቲካዊ መልዕክት በቱርካውያን ፖለቲከኞች ዘንድ መነጋገሪያ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን በበርሊን ተገኝተው ሀገራቸው የምታደርገውን የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ይከታተላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

People are also reading