Home Back

በአውሮፓ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ምን አዳዲስ የታሪክ ክስተቶች ተስተዋሉ?

fanabc.com 2024/10/5

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች አስገራሚ ክስተቶችን አስተናግደው ትናንት ምሽት በተደረጉ ጨዋታዎች ተጠናቀው ወደ ጥሎ ማለፉ የሚገቡ 16 ቡድኖች ተለይተው ታውቀዋል።

ለ13 ቀናት በተደረጉ የምድብ ጨዋታዎች ጥሩ ስብስብ ያላት ክሮሺያ ሳትጠበቅ ከምድብ ስትሰናበት ምስራቅ አውሮፓዊቷ ዩክሬን 4 ነጥብ እያላት ከምድብ ሳታልፍ መቅረቷም ሌላኛው አሳዛኝ ክስተት ሆኗል፡፡

በአንፃሩ ጆርጂያ በመድረኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጥ 16 ውስጥ መግባት የቻለች ሲሆን ኦስትሪያ የሞት ምድብ ከተባለው ድልድል የምድቡ መሪ በመሆን ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለችበት አጋጣሚም ሆኗል፡፡

በተጨማሪም ስሎቫኪያ ረዳት አሰልጣኟ በተመለከቱት ቢጫ ካርድ ምክንያት እኩል ውጤት ካስመዘገበችውን ዴንማርክ ተከትላ ሶስተኛ ደረጃን እንድትይዝ የተደረገበት እንዲሁም በምድብ 5 ሁሉም ቡድኖች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እኩል 4 ነጥብ ያመጡበት አጋጣሚም ተስተውሏል፡፡

ይህንን አስገራሚ ክስተትና አጋጣሚ ያየንበት 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታ የጥሎ ማለፍ ምድብ ድልድል ይፋ ሆኗል፡፡

በዚሀም መሰረት አዘጋጇ ጀርመን ከዴንማርክ፣ ስዊዘርላንድ ከጣሊያን፣ እንግሊዝ ከስሎቫኪያ እንዲሁም ስፔን ከጆርጂያ ይገናኛሉ።

በተመሳሳይ ፈረንሳይ ከቤልጂየም፣ ፖርቹጋል ከስሎቪኒያ፣ ሮማኒያ ከኔዘርላንድስ እንዲሁም ኦስትሪያ ከቱርክ በጥሎ ማለፉ የሚገናኙ ይሆናል፡፡

የጥሎ ማለፉ ጨዋታ በመጪው ቅዳሜ ስዊዘርላንድ ከጣሊያን በሚያደርጉት ጨዋታ የሚጀመር ሲሆን ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ኦስትሪያ ከቱርክ በሚያደርጉት ጨዋታ ፍፃሜውን በማግኘት ሩብ ፍጻሜ የሚገቡ ስምንት ሀገራት ተለይተው ይታወቃሉ።

People are also reading