Home Back

ኤኤንሲ መንግስት ለመመሥረት የሚያስችል ድምጽ አላገኘም

voanews.com 2024/7/2
የደቡብ አፍሪካ የምርጫ ኮሚሽን ብሔራዊ ውጤቶች ኦፕሬሽን ማዕከል
የደቡብ አፍሪካ የምርጫ ኮሚሽን ብሔራዊ ውጤቶች ኦፕሬሽን ማዕከል

በደቡብ አፍሪካ ምርጫ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) እየመራ ቢሆንም፣ መንግስት ለመመሥረት የሚያስችል አብላጫ ድምጽ እንዳላገኘ በመነገር ላይ ነው።

እስከ አሁን ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው ድምጽ የተቆጠረ ሲሆን፣ ላለፉት 30 ዓመታት በገዢ ፓርቲነት የከረመው ኤኤንሲ ከ42 በመቶ በታች ድምጽ እንዳገኘ ከምርጫ ኮሚሽን የሚወጡ አሃዞች ጠቁመዋል።

በመጨረሻው ውጤት ከአምሳ በመቶ በላይ የሚሆነውን ድምጽ እንደማያገኝ በመጠበቅ ላይ ሲሆን፣ ይህም መንግስት ለመመሥረትና ፕሬዝደንቱን ለመሾም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋራ እንዲቀናጅ ሊያስገድደው ይችላል ተብሏል።

ከእ.አ.አ 1994 ጀምሮ በፓርላማ አብላጫ ድምጽ ይዞ በገዢ ፓርቲነት የቆየው ኤኤንሲ፣ በረቡዕ ምርጫ የበርካታ ሕዝብ ድምጽ አጥቷል። በ1994 በኔልሰን ማንዴላ መሪነት ተወዳድሮ 62 በመቶ ድምጽ ማግኘቱ ይታወሳል።

በረቡዕ ምርጫ ‘ዲሞክራቲክ አላያንስ’ 22.64 በመቶ ድምጽ በማግኘት በሁለተኝነት በመከተል ላይ ነው።

የቀድሞው ፕሬዝደንት ጄከብ ዙማ አዲስ ፓርቲ ኡምኮንቶ ዊሲዝዌ (ኤም ኬ) ፓርቲ 12 በመቶ ድምጽ በማኘት ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ይከተላል።

አጠቃላይ ውጤቱ በሳምንቱ መጨረሻ እንደሚታወጅ በመጠበቅ ላይ ሲሆን፣ ፖለቲከኞች በኤ ኤን ሲ መሪነት በሚፈጠር ቅንጅት ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል።

People are also reading