Home Back

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

ethiopianreporter.com 2024/10/6

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል ታሳቢ የሚደረጉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለበጀት ዓመቱ የሚያስፈልገው ገቢ ምንጮች (ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ተሰብሳቢዎች)፣ የውጭና የአገር ውስጥ ብድሮችና ዕርዳታዎች፣ የዕዳ ጫና፣ የመንግሥት ብድር፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትና አጠቃቀም፣ የኤክስፖርት አቅም፣ የገቢና ወጪ ምጥጥንና ሌሎች ጉዳዮች የገንዘብና የፊስካል ሁኔታውን ጤንነት ይወስናሉ፡፡ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ደግሞ በዜጎች ፍትሐዊ የዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢና ኑሮ ላይ ይንፀባረቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አጠቃላዩ የፍጆታ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ዋጋ ቅናሽ የማሳየት አዝማሚያ እንዳለው ሪፖርት ቢደረግም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ተግዳሮትና ከአቅም በላይ እየሆነ ያለው የምግብ ዋጋ ንረት ነው፡፡ ከሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች በተጨማሪ የምግብ ዋጋ ንረት የብዙዎችን ሕይወት እያናጋ ነው፡፡

የመጪውን ዓመት ረቂቅ በጀት መግለጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ያብራሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ‹‹የአጠቃላይ የፍጆታ ዕቃዎችና አገልግሎቶች የዋጋ ዕድገት በበጀት ዓመቱ የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ ቢሆንም፣ ለተወሰነ ጊዜ ባለሁለት አኃዝ ሆኖ እንደሚቀጥል ግምት ተወስዷል። ለዚህም ጥብቅ የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲ ዕርምጃዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉና አማካይ የዋጋ ንረት አሁን የግንቦት ወር መጨረሻ ካለበት 27.4 በመቶ በቀጣዩ በጀት ዓመት ወደ 12 በመቶ ዝቅ እንደሚል ታሳቢ ተደርጓል፤›› ብለው ነበር፡፡ በተደራራቢና ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ምክንያት በኢኮኖሚ ማሻሻያው ካልተቀረፉ ተግዳሮቶች መካከል አንዱና ዋናው የዋጋ ንረት መሆኑን፣ በቅርብ ወራት የዋጋ ዕድገት መጠነኛ ቅናሽ እያሳየ የመጣ ቢሆንም ወደ አንድ አኃዝ ዕድገት እንዲወርድ ማድረግ አለመቻሉን፣ ምንም እንኳን መንግሥት አስፈላጊ የሆኑ የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም የዋጋ ንረትን የሚፈለገው ደረጃ ማውረድ ማዳገቱን አስታውቀዋል፡፡

ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በአቅርቦት ረገድ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተገቢ እንደሆነ እንደሚታመን ተናግረዋል፡፡ በአንፃሩ ረዥም የአቅርቦት ሰንሰለት መኖር፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ውስንነት፣ የነዳጅ ዘይትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መናር፣ እንዲሁም በቀይ ባህር የንግድ መተላለፊያ መስመር ላይ የሚታዩ እክሎች የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እየተገዳደሩ ናቸው ብለዋል፡፡ በመዋቅራዊና መፍትሔያቸው በመንግሥት እጅ ባልሆኑ ምክንያቶች የሚከሰተውን የዋጋ ጭማሪ ለማስቆም አሁንም ጊዜና ብርቱ ትግል የሚጠይቅ መሆኑን አውስተዋል። ለፊስካል ጉድለት መሸፈኛ የሚወሰዱ ብድሮችን በመገደብም ሆነ ብድሮቹ ሲወሰዱ የዋጋ ንረትን የማያስከትሉ የብድር ዓይነቶችን ጥቅም ላይ በማዋል፣ ከዚህ ምንጭ ሊመጣ የሚችለውን የዋጋ ንረት መገደብ በኢኮኖሚ ማሻሻያው የተያዘ አንዱና ትልቁ ዕርምጃ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም የገንዘብ ፖሊሲውን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት በረጅም፣ በመካከለኛና በአጭር ጊዜ ውስጥ በቅደም ተከተል ሊወስዳቸው የሚችሉ ዕርምጃዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁን ፋታ አልሰጥ ያለውን የምግብ ዋጋ ንረት ግን በፍጥነት መፍትሔ ለመስጠት መረባረብ ይኖርበታል፡፡ የዜጎች ገቢና ወጪ መመጣጠን አቅቶት የምግብ ዋጋ ንረት ብዙዎችን እየፈተነ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፣ ለችግሩ ተገቢውን ዕርምጃ ለመውሰድ በጥናት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ምግብ አንዱና ዋነኛው ችግር ሲሆን በተለይ በከተሞች የመኖሪያ ቤት ኪራይ፣ የኤሌክትሪክና የውኃ ፍጆታ ታሪፍ፣ የልጆች ትምህርት ቤት ክፍያና ተያያዥ ወጪዎች የብዙዎችን ኑሮ ሲኦል እያደረጉ ነው፡፡ የአገሪቱ የግብይት ሥርዓት ፈሩን በመሳቱ በምግብ ምርቶችና ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት በዋናነት ሰው ሠራሽ ቢሆንም፣ በፀጥታ ችግር ምክንያት የአቅርቦት መስተጓጎል ደግሞ የራሱ ድርሻ አለው፡፡ አስመራሪውን የዋጋ ንረት ለማርገብ የሚረዱ መፍትሔዎች ይታሰብባቸው፡፡

አማካይ 27.4 በመቶ የዋጋ ንረትን በመጪው በጀት ዓመት ወደ 12 በመቶ ዝቅ እንደሚል በመንግሥት ታሳቢ መደረጉን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አስረድተዋል፡፡ የዋጋ ንረቱን በዚህ መጠን ለማውረድ ግን ከፍተኛ የሆነ ጥረት እንደሚያስፈልግ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ የፀጥታ ዕጦትና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮት ውስጥ ላለች አገር ይህ ሐሳብ ከበድ ይላል፡፡ በትግራይ ክልል የነበረውን ጦርነት የገታው የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ መሆን፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄደው ውጊያ መቋጨት፣ በተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ዕገታዎችና የሰላም ማደፍረሶች መቆም፣ እንዲሁም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድናት፣ በቱሪዝም፣ በትራንስፖርትና በመሳሰሉት ዘርፎች የሚስተዋሉ ከቢሮክራሲና ከፀጥታ ጋር የተያያዙ ችግሮች መቀረፍ አለባቸው፡፡ በሁሉም ክልሎች ምርትና ምርታማነት ላይ በማተኮር ሰፋፊ ሥራዎች መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚስተዋሉ ችግሮች ሲቀረፉና ሰላም ሲሰፍን ምኞቱ ሊሳካ ይችላል፡፡

ባለፈው ሳምንት በተካሄደ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ፣ በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ የመንግሥት ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ ምሳ መብላት አይችሉም የሚለው ይገኝበታል፡፡ የምሳ ሰዓታቸውን ወደ እምነት ተቋማት በመሄድ እንደሚያሳልፉም ተሰምቷል፡፡ መንግሥት እንዲህ ዓይነት አጣዳፊና ጊዜ የማይሰጡ ችግሮች እንዴት መቀረፍ እንደሚኖርባቸው ሊያስብበት ይገባል፡፡ የምግብ ችግርን ለመፍታት የሚያግዙ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ከየትም ይምጡ ከየት መደመጥ አለባቸው፡፡ የመጪውን ዓመት በጀት ከታክስ ለማሟላት ዕቅድ ሲያዝ የታክስ ከፋዩ ሕዝብ የኑሮ ሁኔታም ሊጤን ይገባዋል፡፡ ታክስን አስመልክቶ በተለያዩ ወገኖች የሚቀርቡ ሐሳቦች ቢደመጡ በርካታ ጠቃሚ ነገሮች ይገኙባቸዋል፡፡ የምግብ ነገር ጊዜ የማይሰጥ ስለሆነ ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ ይሰጠው፡፡ ችግሩ ከአቅም በላይ ስለሆነ የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

People are also reading